Fana: At a Speed of Life!

ከተሜነትን ያላበሰው የከተማ ልማት…

የከተማ ልማት የአንድን ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መሠረተ-ልማታዊ መዋቅር በማዘመን የዜጎችን የመኖሪያ እና የሥራ አካባቢ ምቹ የማድረግ የተቀናጀ ሂደት ነው።

በፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ የተባለለትን የከተሞች የመዋቅር እና የገፅታ ለውጥ እያስተናገደች ትገኛለች።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ፣ የከተማ ልማት ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።

መንግሥት ከተሞችን የዕድገት፣ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ የጀመራቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ከተሞች ገፅታ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ተጀምሮ አሁን ላይ ወደ ተለያዩ የክልል ዋና ዋና ከተሞች የተሻገረው የኮሪደር ልማት፣ በኢትዮጵያ የከተማ ልማት ታሪክ ትልቅ እመርታ ነው።

በኮሪደር ልማቱ ጠባብ የነበሩ መንገዶች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰፉና ለትራፊክ ፍሰት ምቹ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟሉ ሰፋፊ የእግረኛ መሄጃዎች፣ የሳይክል መስመሮች እና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሠረተ-ልማቶች ተገንብተዋል።

ለከተማ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች የሚሆኑ ዘመናዊ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች እና ማረፊያ ወንበሮች በየኮሪደሩ ተደራሽ ሆነዋል።

ከተሞችን ተስማሚና ውብ የመኖሪያ አካባቢ የማድረግ ስትራቴጂ አካል የሆኑ በርካታ ግዙፍ የፓርኮች እና የአረንጓዴ ስፍራዎች ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል፡፡

በዚህ ሥራ የአንድነት፣ የእንጦጦ፣ የሸገር እና የሳይንስ ሙዚየም ፓርኮች ተገንብተው ለሕዝብ ክፍት ሆነዋል።

ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ወደ ውብ መዝናኛና የቱሪስት መስህብነት ተለውጠዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በከተሞች ውስጥ በመተከላቸው የከተሞች የአየር ንብረት እና የአረንጓዴ ሽፋን እንዲሻሻል አድርጓል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ያለ ሲሆን፣ በከተሞች የመኖሪያ ቤቶች ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት የነዋሪውን የቤት ፍላጎት ለማሟላትም እንዲሁ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዘመናዊ የትራንስፖርት መሠረተ-ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መጨናነቅን ለመቅረፍ እና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት የተሰሩ ሥራዎችም እመርታ አሳይተዋል፡፡

በከተማ ልማት ሥራው ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ የኤሌክትሪክ የሕዝብ ትራንስፖርት አውቶቡሶችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል፡፡

የትራፊክ ፍሰቱን በቴክኖሎጂ ለመምራት የሚያስችሉ የስማርት ትራፊክ ቁጥጥር ዘመናዊ መብራቶችና የካሜራ ሥርዓቶችም ተዘርግተዋል።

በከተሞች የከተማ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍና ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ ዲጂታላይዜሽን በስፋት እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የነዋሪዎች መታወቂያ እና የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሥርዓቶች ወደ ዲጂታል በመቀየራቸው ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል።

በአንድ ማዕከል አገልግሎት የንግድ ፈቃድ፣ የግብር ክፍያ እና የፍጆታ አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲከፈሉ ተደርጓል።

በአጠቃላይ የከተማ ልማት የከተሞችን ውበትና ምቾት ከመጨመሩ በላይ፣ ለዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ችሏል፡፡

የከተማ ልማት ከምቾትና ከውበትም በላይ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት መለኪያም ስለሆነ ነው ነገን ታሳቢ በማድረግ በጥንቃቄና በዕቅድ እየተተገበረ ያለው።

በኢትዮጵያ የተጀመረው ከተማን የማዘመን ሥራ፣ ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ የነዋሪዎችን የማኅበራዊ ሕይወት ባገናዘበ መልኩ እየተሠራ ነው፡፡

ሥራውም አካባቢን የማይበክል እና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ ተደርጎ እየተተገበሩ ይገኛል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.