Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተለያዩ የንግድ ህግ ጥሰት በፈፀሙ 159 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የንግድ ህግ ጥሰት በፈፀሙ 159 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
እርምጃ የተወሰደው ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ ምክንያት በማድረግ ያለ ህጋዊ ደረሰኝ እና ያለ ህጋዊ ንግድ ፍቃድ ሲነግዱ፣ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፣ ህገ ወጥ ምርት ያከማቹ እና የደበቁ በጠቅላላው የተለያዩ የንግድ ህግ ጥሰት በፈፀሙ 159 የንግድ ተቋማት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ህገ-ወጥ ንግድና የዋጋ ቁጥጥር ግብረ ሀይል ስምሪት አፈፃፀም በተመለከተ ከአስሩ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደገለጹት÷ በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ በከተማዋ የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳይከሰት እና የንግድ ህግ ጥሰት እንዳይፈጸም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ከ81 በላይ የተደራጀ ግብረ ሀይል ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ግብረ ሀይሉ ባለፉት ቀናት ባካሄደው የንግድ ክትትል እና ቁጥጥር ስራም የንግድ ህግ ጥሰት በፈፀሙ 159 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የገለጹት አቶ አብዱልፈታ ህገ-ወጥ ምርት ያከማቹ እና የደበቁ 19 መጋዘኖች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷልም ብለዋል፡፡
በድጎማ በሚቀርቡ እና ከቀረጥ ነፃ በገቡ ምርቶች በተተመነላቸው ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ የማረጋገጥ ተግባርም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አቶ አብዱልፈታ መጠቆማቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.