በመዲናዋ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከ118 ኪ.ሜ በላይ ርዝመት ያላቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ውል ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከ118 ኪ.ሜ በላይ ርዝመት ያላቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ውል ተፈራረመ፡፡
ባለስልጣኑ ከ118 ኪ.ሜ በላይ ርዝመት ያላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ነው ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በዛሬው ዕለት ውል የተፈራረመው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው የውል ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡
ግንባታቸውን ለማካሄድ የኮንትራት ውል ከተገባላቸው 8 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 50 ኪ.ሜ የሚሆነው በአስፋልት ኮንክሪት የሚሰራ ሲሆን ቀሪው 68 ነጥብ 4 ኪ.ሜ የሚሆነው ደግሞ በኮብል ንጣፍ የሚከናወን ይሆናል ተብሏል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ በአማካኝ ከ12 እስከ 19 ወራት የተያዘላቸው ሲሆን ለግንባታ ወጪያቸውም ከ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ እንደተመደበላቸው ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ገለጸዋል ፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶች በቦሌ አራብሳ፣ በየካ ጣፎ፣ በጀሞ ጋራ ፣በኮዬ ፈጬ እና በጨፌ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢዎች የሚገነቡ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ 11 እስከ 38 ነጥብ 9 ኪ.ሜ የሚደርስ ርዝመት እንዳላቸውም ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ለጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ጥራታቸውን ጠብቀው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ የመንገድ ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የኮንትራት ጊዜ በጥራት አጠናቆ ለማስረከብ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡