መንግስት በመተከል ዞን የተከሰተውን አለመረጋጋት በአስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተፈናቃይ ወገኖች ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነበሩበት ቀየ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ በመኖራቸው ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውን በመተከል ዞን በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች አስታወቁ፡፡
በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ ከኩጅ ቀበሌ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉት ወገኖች መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
እነዚህ ተጎጂ የማህበረሰብ ክፍሎች በመንግስት እና በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አማካኝነት የሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጸው÷ ይህ በቂ ባለመሆኑ ወደ ነበሩበት ቀየ እንዲመለሱና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራው መጠናከር እንዲጠናከርም ነው የጠየቁት።
በቀጠናው አንጻራዊ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ በሚመለከተው አካል በኩል ጥበቃ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውንም ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቡለን ወረዳ ብቻ ከ40 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ሲሆን÷ በአጠቃላይ በዞኑ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።