ሁለንተናዊ ሚናዋን እያሳደገች ያለች ሀገር…
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትውፊትና በዲፕሎማሲያዊ ታሪኳ የበርካታ ታዋቂ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መስራች አባል በመሆን ቀዳሚና ታሪካዊ ሀገር ናት።
የረጅም ዘመናት ነፃነቷ በአፍሪካና በዓለም መድረክ የጥቁር ሕዝቦች ድምፅ እንድትሆን አስችሏታል።
በዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት የራሷን አሻራ እያኖረች ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡
የቀድሞው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የኢጋድ፣ የኮሜሳ እና የብሪክስ አባል ሀገር ናት፡፡
ኢኮኖሚዋን ይበልጥ ከዓለም ገበያ ጋር ለማስተሳሰርም የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ ይህ የኢትዮጵያን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂካዊ ሚና ያሳያል፡፡
በተቋማት ካላት የመስራችነት፣ የአባልነትና የተሳትፎ ሚና በዘለለ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በሰላም ማስከበርና በቀጣናዊ ትስስር ያላትን ተሳትፎም ማየት የግድ ይላል፡፡
ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሚናዋ ሲቃኝ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1923 ሊግ ኦፍ ኔሽንስን ተቀላቀለች፡፡ ተቋሙ ተዳክሞ ሚናው በተባበሩት መንግሥታት ሲተካ 1945 ከድርጅቱ 51 መስራች አባል ሀገራት መካከል አንዷ እና ብቸኛዋ ነፃ ጥቁር አፍሪካዊት ሀገር ነበረች።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመስረት ጋር ተያይዞ የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት (ICJ) ስምምነት ሲጸድቅ ኢትዮጵያም ከመስራቾቹ አንዷ ነበረች።
1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) አዲስ አበባ ላይ እንዲመሰረት ቀዳሚውን ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ስትሆን በአሁኑ ወቅትም የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ ናት።
የቀድሞዎቹን ከብዙ በጥቂቱ በዚህ ደረጃ ካየን ኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የኢኮኖሚና የፖለቲካዊ ጥምረቶች መስራችና አባል ሀገርም ናት፡፡ ኢትዮጵያ እያደጉ ያሉ ሀገራትን የያዘውን የብሪክስ ጥምረትን በይፋ የተቀላቀለች ሲሆን፣ በዚህም በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካ መድረክ ላይ ያላትን ተጽዕኖ እያሳደገች ትገኛለች፡፡
በተጨማሪም የንግድ ሥርዓቷን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት ለመግባት የምታደርገውን የብዙ ዓመታት የድርድር ሂደት ለማጠናቀቅ በንቃት እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያ አሁንም ቀጣናዊ ትስስርና የደኅንነት ሚናዋን ለመወጣት በትጋት እየሰራች ያለች ሲሆን፣ ይህንንም በሰላም ማስከበር፣ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥት እና በመስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ ማየት ይቻላል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ቀዳሚ የሰላም አስከባሪ ኃይል ላኪ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሀገር ናት፡፡ ይህንንም በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ እና በሱዳን/ደቡብ ሱዳን ተወጥታለች፡፡
በቀጣናው ሰላም፣ ፀጥታና ልማት ላይ በሚሰራው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን በሊቀመንበርነትና በአባልነት ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ የኢኮኖሚ ትስስርንና ንግድን ለማጠናከር ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ትሰራለች።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በምታደርገው ትብብር የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እየተገበረች ትገኛለች፡፡ በዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ መስራች አባል ሀገር ናት፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከእነዚህ ተቋማት ጋር የፋይናንስና የቴክኒክ ትብብር ታደርጋለች።
በተቋማት ካላት የመስራችነትና የአባልነት ሚና በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እየተጫወተች ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እንደ አርአያ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሀገሪቱ የኮፕ (COP) የአየር ንብረት ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ጭምር እንድትመረጥ እያደረጋት ነው፡፡
ከተባበሩት መንግሥታት ጋር እስከ 2030 የሚዘልቅ የዘላቂ ልማት ትብብር ማዕቀፍ (UNSDCF) በመፈራረም በምግብ ዋስትና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በትብብር እየሰራች ነው።
ኑ፤ ሀገር እንሥራ!