በመተከል ዞን ለሽፍቶች መሳሪያ ሲያቀብሉ የነበሩ ቤተሰቦቹን ለህግ አሳልፎ የሰጠው ወጣት
አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) በመተከል ዞን ለሽፍቶች መሳሪያ ሲያቀብሉ የነበሩ ቤተሰቦቹን ለህግ አሳልፎ የሰጠው ወጣት “እናቴ ብትሞትም ያለምንም ልዩነት ተንከባክቦ ያሰደገኝ የአካባቢው ማህበረሰብ ነው” ይላል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተደራጁ ሽፍቶች በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ሌሎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ወጣት ሙሉጌታ አንተነህ ሺሊ ችግሩ ከተፈጠረባቸው የመተከል ዞን ወረዳዎች አንዷ በሆነችው በዳንጉር ወረዳ አዛርቲ-ትክሊ ቀበሌ ነዋሪ ነው።
ተወልዶ ባደገበት መንደር ከየተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በሰላምና በፍቅር አብሮ ማደጉን ያስታውሳል።
ሙሉጌታ ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ እናቱ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ህይወታቸው ቢያልፍም የአካባቢው ማህበረሰብ እንደ ወላጅ ሆኖ ያለ ችግር አሳድጎ ለወግ ማእረግ እንዳበቃውም ይገልፃል።
አሁን ላይ ግን ልዩነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በተሰራ የፖለቲካ ሴራ ረዥም ዘመን አብረው በኖሩ ዜጎች ላይ አሳዛኝ ጥቃት በመፈፀሙ ከባድ ሃዘን እንደገባው ይናገራል።
ጥቃት ለማድረስ ሴራው ረዥም ጊዜ ወስዶ በተደራጀ መልኩ የተሰራበት መሆኑንም ይናገራል።
በኢንቨስትመንት ስም በአካባቢው በተሰማሩ የህወሃት ቡድን አባላት የሰለጠኑና የጥፋት ተልዕኮ የተሰጣቸው ወጣቶች ጥቃቱን መፈፀማቸውን ነው የገልጸው።
ጁንታው መቀሌ መመሸጉን ተከትሎ በዞኑ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶች ቀስ በቀስ እየሰፉና የሚያስከትሉት ሰብዓዊ ቀውስም እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
በቅርቡ በመተከል ዞን በተፈጸመው ጥቃትም በዞኑ በሚኖሩ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ጉዳት መድረሱን ወጣት ሙልጌታ ይናገራል።
ጥቃቱ በጥቅም የተደለሉ ህገ-ወጥ ቡድኖ የፈፀሙት እንጂ የጉሙዝ ማህበረሰብን እንደማይወክልም ገልጿል።
በተፈጸመው ጥቃት ሙሉጌታ ወላጅ አባቱን ጨምሮ ስምንት ዘመድና ቤተሰቦቹ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉበት ይናገራል።
በተጨማሪም ከህገ-ወጥ ቡድኑ ጋር አልተባበርም ያሉ በርካታ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ላይ ጥቃት ተፈፅሟል ይላል።
የጉዳቱን ስፋትና አስከፊነት በትክክል ለመረዳት የጥቃቱን ሰለባዎች በቅርበት መገንዘብ እንደሚገባም የሚናገረው ወጣት ሙልጌታ÷ለጥፋት ቡድኑ መሳሪያ ሲያቀብሉ የነበሩ ሶስት የቤተሰብ አባላቱን ተጠያቂ እንዲሆኑ ለህግ አሳልፎ መስጠቱን ገልጿል።
እሱ የፈፀመውን ተግባር በመከተል ሌላው የአካባቢው ማህበረሰብም ወንጀለኞችን ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል ብሏል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የጥቃቱን ትክክለኛ ገጽታ የማሳወቅ ሃላፊነት እንዳለበትና ማህበረሰቡ በይቅርባይነትና እርቅ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርቧል።
መንግስት ከህግ ማስከበር ስራው ጎን ለጎን የህዝብን አብሮነትና መቀራረብ የሚያጎለብቱ ተግባራትን ማከናወኑን ሊቀጥል ይገባዋል ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጸጥታ ሁኔታ የሚመራ ግብረ-ሃይል በፌዴራል መንግስት ተቋቁሞ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ ሲሆን አሁን ላይ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ ይታወቃል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!