ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 200 ኦፊሰሮች አሰመረቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 200 ኦፊሰሮች አስመረቀ።
የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመሰገን ጥሩነህ ተመራቂዎቹ የሀገር ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርገውን የተሳካ ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ እገዛ እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።
ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ያካበተውን የረጅም ጊዜ ልምድ በመቀመር ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅቶ ስልጠና መስጠት መጀመሩ የሚያኮራ የለውጥ ተግባር መሆኑን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።
የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ለሁለት ወራት በአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 200 ጀማሪ ኦፊሰሮችን በዛሬው ዕለት ባስመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የአቪዬሽን ደህንነት ባለሙያዎችን ዓለም አቀፍ መሥፈርት በጠበቀ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ማሠልጠኑ ኢትዮጵያን በዘርፉ ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ተመራቂዎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች የተመለመሉና በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ቆይታቸውም ለሁለት ወራት በአቪዬሽን የደህንነት ኪነሙያ ስልጠና በመውሰድ በዛሬው ዕለት የምስክር ወረቀት ተበርክቷላቸዋል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመሰገን ጥሩነህ እንዳሉት ተመራቂዎቹ፤ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ጠንካራ ሥልጠና የተሠጣቸው ሲሆን፤ የሀገር ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርገውን የተሳካ ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
በአቪዬሽን ዘርፉ አገልግሎታቸውም ትህትናን፣ እውቀትን፣ ክብርንና ታማኝነትን በመላበስ ሀገራቸውንና ህብረተሰባቸውን ማገልገል እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የአቪዬሽን ደህንነት ባለሙያዎቹ ሀገሪቱ ላይ ሊቃጣ የሚችል የሽብር ጥቃትንና የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመመከት በኩል የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነትና የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ዳይሬክተር ጀነራሉ አሳስበዋል።
የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት አቶ ወንድወስን ካሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በአቪዬሽን ደህንነት መስክ ጥራት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት፤ ተጨባጭ፣ ዘመናዊና ወቅታዊ እንዲሁም አካበቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ሥልጠና በመስጠት የዘርፉን የአገልግሎት ብቃት ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ባገኘው እውቅና መሠረት በደህንነት ፣ በኢንተለጀንስ፣ በስትራቴጂክ ጥናትና በቋንቋ የትምህርት መስኮች በዲግሪና በዲፕሎማ ስልጠና ለመስጠት ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አቶ ወንድወሰን አያይዘው አብራርተዋል።
ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃና ደህንነት መስክ ስልጠና በመስጠት ከአርባ አመታት በላይ የዘለቀ ልምድ ያለው ሲሆን÷በ2011 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንዳደገ ተቋሙ ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!