Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን የመጥለፍ ሴራ ከመጎንጎን የማያርፈው የካይሮ ፖለቲካ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከካይሮ የሚወጡ ድምፆች ቁጥራቸው እየጨመረ፣ ድምፃቸውም እየጎላ መጥቷል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባድር አብደላቲ በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ምንም ዓይነት የወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የለባትም ሲሉ ይደመጣሉ።
ከዚህ ቀደም የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ በዘ ናሽናል ሚዲያ ቀርበው በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት የመክፈት አማራጭ ከጠረጴዛው አልተነሳም ማለታቸው ይታወሳል።
ከሰሞኑ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በ አህራም ኦንላይን እና ኢጂፕት ኤክስፕረስ በኩል የካይሮን ሴራ ግልፅ ያደረገ ሀሳብ አንጸባርቀዋል።
ባድር አብደላቲ ያንፀባርቁት አቋም፣ ካይሮ አዳዲስ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ህብረቶችን በመፍጠር ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ያላትን ተቀባይነት፣ ግስጋሴ እና ወሳኝ ሚና የመገደብ ውጥንን ነው።
ግብፅ ለአስርት ዓመታት በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ የነበራትን የውሃና የባሕር መስመር ኢፍትሃዊ ድርሻ የማጣት ፍርሃት አድሮባታል።
አያቶቻቸው የዘረጉት ኢትዮጵያን ከውሃ አካላት የማራቅ’ የቆየ ስትራቴጂ ዛሬ ከዘመናዊው የፖለቲካ እውነታ ጋር እየተጋጨ መጥቷል። ኢትዮጵያም ፍትሐዊ አጠቃቀምና ድርሻ እውን ይሆን ዘንድ የምትሰራው ስራ ተቀባይነት እያገኘ ነው።
ዛሬ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የካይሮን የታሪክ ፍርሃት እና ሴራ መለየት ጀምሯል። የግብፅ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎችና የፖለቲካ ጫናዎች የቀጣናውን እውነተኛ ችግር ከመፍታት ይልቅ ውጥረቱን የሚያባብስ መሆኑን አስረግጠው የሚናገሩም ተበራክተዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚኖራት አወንታዊ ሚና ለቀጣናው መረጋጋት አስፈላጊ እንጂ ስጋት አለመሆኑንም ሽንጣቸውን ገትረው ከሚከራከሩት ውስጥ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች የደህንነት ዳይሬክተር ካሜሩን ሃድሰን አንደኛው ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ባለቤት፣ በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ ያላት ሀገር የራሷ የሆነ የባሕር በርና የወታደራዊ የንግድ እንቅስቃሴ ፍላጎት ማሳየቷ ለካይሮ የስትራቴጂ ሚዛን መዛባት መስሎ ታይቷታል።
ይህ ግን የኢትዮጵያ የህልውናና የኢኮኖሚ ጥያቄ እንጂ የሌሎችን ጥቅም የመጋፋት ፍላጎት አይደለም፡፡
በሔብሮን ዋልታው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.