Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልልን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር ያስፈልጋል -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የትግራይን ክልልን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ዛሬ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም በመቀሌ ከተማ የሚገኙትን የዓይደር ስፔሻላይዥድ ሆስፒታል፣ የፌደራል መንግስት እህል ማከማቻ ማዕከላዊ መጋዘን እና በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡

ፕሬዘዳንቷ ከመቀሌ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋርም ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱም የአገር ሽማግሌዎች በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የተንሰራፋው የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ፣ ከመንግስት ቢሮዎች የተዘረፉ ቁሳቁሶች ተሟልተው በተጠናከረ መልኩ ስራ እንዲጀምሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በትግራይ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ለሰላም እና ለጤና ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰጡት ምላሽም ትግራይን ወደቀደመው ሰላም ለመመለስ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡

የትግራይ ክልልን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጎን በመሆን ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በትግራይ ክልል መንግስት ህዝብ አብሮ የሚኖርበትንና የሚደጋገፍበትን ስርዓት በመገንባት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያሉ የሕዝብ ጥቄዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እየተሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ትግራይን መልሶ ለማደራጀት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ያስረልጋል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ በመቀሌ ያደረጉትን ጉብኝት በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በትናትናው ዕለት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር በትግራይ ክልል እየተሰጠ የሚገኘውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለመመልከት በመቀሌ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.