ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በድንበር ደህንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማጎልበት በድንበር ደህንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ኃይል ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ ተፈራርመውታል።
ስምምነቱ ትኩረት ካደረገባቸው የድንበር ደህንነት ጉዳዮች በተጨማሪ ብቃት ያላቸው የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ የፖሊስ አባላት ማፍራትን ዓላማ ማድረጉም ነው የተገለጸው።
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ ወገኖች በፖሊስ ሰላም ማስከበር፣ በፎረንሲክ ሳይንስ፣ በትምህርትና በሰው ኃይል ስልጠና ላይ የሚተባበሩ ሲሆን÷ በድሬዳዋ እና በጅቡቲ የጋራ ግብረ ኃይል ለማቋቋምም ስምምነት ላይ ተደርሷል ፡፡
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በየስድስት ወሩ በዘርፉ በከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ምክክር ለማድረግም ተስማምተዋል፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ እንደተናገሩት÷ ስምምነቱ ሁለቱ ወንድማማች ሃገራት በደህንነት እና በፖሊስ መስክ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋልም ነው ያሉት።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ አያይዘውም በተደጋጋሚ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍም የመግባቢያ ሰነዱ ወሳኝነት አለው ብለዋል።
ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ በበኩላቸው በአጭር ጊዜ ለዚህ ስምምነት መብቃታቸው ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽን አመስግነው÷የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ተግባር መለወጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በፊርማ ስነስርዓ ላይ በጂቡቲ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች መገኘታቸውም ነው የተገለጸው ፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኮሚሽነር ደመላሽ እና በኮሎኔል አብዱላሂ መካከል የተደረገውን ስብሰባ ተከትሎ መሆኑን ጅቡቲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!