Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች በመፍታት የጀመረችውን ልማት አስጠብቃ የመቀጠል አቅም አላት-የቻይናው ታሂ ኢንስቲቲዩት

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ያጋጠሟትን ችግሮች በመፍታት የጀመረችውን ልማት አስጠብቃ የመቀጠል አቅም አላት ብለው እንደሚያምኑ የቻይና የምርምርና ሀሳብ አመንጪ ተቋም የሆነው የታሂ ኢንስቲቲዩት የስራ ሃላፊዎች ገለፁ።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በቻይና ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆነው የታሂ ኢንስቲቲዩት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ከቻይና አፍሪካ ኢንስቲቲዩት ተመራማሪዎች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደሩ በትግራይ ክልል በነበረው ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በህዝቡ ላይ የደረሱ ሰብዓዊ ጉዳቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ እርዳታዎችን የማሰራጨትና የመሰረተ ልማት አውታሮችን የመጠገን ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በውጭ ሚዲያዎች ከሚነገረው በተቃራኒ በመሬት ላይ የሰብዓዊ እርዳታ ሥርጭት በአግባቡ እየተካሄደ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የድርድር ሂደትን በተመለከተም ኢትዮጵያ ከጅምሩ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ፍትሀዊ አጠቃቀም እንዲኖር አበክራ ስትሰራ የቆየች መሆኗንና የድርድር ሂደቶቹም ፈር እንዲይዙ በማድረግ ረገድ የድርሻዋን መወጣቷን ተናግረዋል።

ሆኖም ግብፅ የራሷን ጥቅም ብቻ ለማስከበር በተከተለችው አፍራሽ አካሄድ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሱዳንም የግብፅን የተሳሳተ አካሄድ በመከተሏ ድርድሮቹ የተፈለገውን ያህል ሊሳኩ አለመቻላቸውን አብራርተዋል።

እንዲሁም ሱዳን በትግራይ የተፈጠረውን ሁኔታ ተከትሎ ሁለቱን ሀገራት በሚያዋስነው ድንበር በተፈጠረው የደህንነት ክፍተት በመጠቀም ከ40 እስከ 50 ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት የኢትዮጵያን መሬት መያዟን አንስተዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የጣሰና በዓለም-አቀፍ ህግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተው ጉዳይዩን በውይይትና በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኗንም አስረድተዋል።

የታሂ ኢንስቲቲዩት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የቻይና አፍሪካ ኢንስቲቲዩት ተመራማሪዎች ገለፃው ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው በመግለፅ ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ ያለች ሀገር እንደመሆኗ አሁን የተፈጠሩት ችግሮች የሚጠበቁ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያም ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የጀመረችውን ልማት አስጠብቃ የመቀጠል አቅም ይኖራታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ቻይናም ሁሉም ሀገር ለውስጥ ችግሮቹ የራሱ መፍትሔ ሊያበጅለት እንጂ በሌላ አካል ጫና እንዲደረግ አትፈልግም ብለዋል።

በትግራይ ያለው ሁኔታ ውስጣዊ የሀገሪቱ ጉዳይ መሆኑን እንደሚረዱ፤ ኢትዮጵያም ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አቅም እንዳላት እንደሚገነዘቡና በዚህም ረገድ የቻይና መንግስት የኢትዮጵያን አቋም በመደገፍ ያሳየው አጋርነት ከመርህ አኳያ ትክክል ነው ብለው እንደሚያምኑ መግለፃቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

 

ኢትዮጵያና ቻይና በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ካላቸው ጠንካራ ግንኙነት በተጨማሪ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር በተሻለ ከፍ በማድረግ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.