ህዝቡን ይዘን ኢትዮጵያን እናሻግራለን – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‘‘ህዝቡን ይዘን ኢትዮጵያን እናሻግራለን’’ ሲሉ በጅማ ስታዲየም የብልጽግና የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ተገኝተው ተናግረዋል፡፡
የጅማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለብልፅግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አክብራችሁ በጠዋት እዚህ ተገኝታችሁ አቀባበልና ድጋፍ ላደረጋችሁልኝ የጅማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አመሰግናለሁ” ብለዋል።
ህዝቡን ይዘን ኢትዮጵያን እናሻግራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆን የማናሸንፈውና ድል የማናደርገው ፈተና የለምም” ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅማ ከተማ ባደረጉት ንግግር ከአመት በፊት ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚያፈርሷትን እናፈርሳለን ብለን ነበር ብለዋል፡፡
“አሁን የኢትዮጵያን አንድነት አረጋግጠን ትኩረታችን የአፍሪካን ቀንድ የአፍሪካ ክንድ ማድረግ ነው” ብለዋል በንግግራቸው።
ኢትዮጵያን ከመፍረስ ያዳነው ሀይል ነገ የአፍሪካን ቀንድ የአፍሪካ ክንድ ያደርጋታል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የእኛ ስልጣን እንደሚያልፍ አውቀን በታማኝነት እና ትጋት እናገለግላለንም” ነው ያሉት።
“በቀጣዩ ሰኞ ምርጫ እናደርጋለን ዛፍም እንተክላለን በዚህም መላው ዓለም ይጋጫሉ ብሎ ሲጠብቅ እናስተምራለን” ሲሉም ተናግረዋል ።
በምርጫው የሚፎካከር የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት የሚያከብር የትኛውም ፓርቲ መልካም እድል እንዲገጥመውም ተመኝተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጫፍ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ መሀል በማምጣት ሀገሪቷን ከውድቀት ለታደጉና በአዲስ ጎዳና እንድትጓዝ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች ቆራጥ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
ብልፅግና በፈተና ውስጥ ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል 1ሺህ 11 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል፡፡
በአላዛር ታደለ እና በሙክታር ጠሃ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!