Fana: At a Speed of Life!

አልማ 21 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ለመሠብሰብ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ልማት ማኅበር ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት ሦስት ዓመታት 21 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ለመሠብሰብ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ማኅበሩ እስከ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም ድረስ የሚካሔደውን የአልማ ሳምንት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የአልማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሐሚድ አሕመድ በሰጡት መግለጫ፥ ማኅበሩ በሳምንቱ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ከመደበኛ አሠራር በተለየ መንገድ የማኅበሩን ሕዝባዊ መሠረት ያሰፋል፤ አዳዲስ አባላት የማፍራት ሥራ ይሠራል፤ ሃብት ይሰበሰባል እንዲሁም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለተጠቃሚዎች ያስረክባል ነው ያሉት ።

ማኅበሩ ትውልድን ማብቃት ይቻል ዘንድ ለትምህርት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል ።

ማኅበሩ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት ሦስት ዓመታት 21 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ለመሠብሰብ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ቢታቀድም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ በጸጥታ ችግር፣ በጎርፍ በሌሎች ችግሮች ምክንያት ማሳካት የተቻለው 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት፥ በተሰበሰበው ገቢ 4 ሺህ 697 የትምህርት፣ የጤና እና የሥራ እድል ፈጠራ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም አቅዶ 1 ሺህ 731 ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ተችሏል።

ከእነዚህ ውስጥም 1 ሺህ 691 ፕሮጀክቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እንደሆነ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በ2017 ዓ.ም የክልሉ ሕዝብ በራሱ እና በልማት አጋሮቹ የልማት ችግሮቹን ቀርፎ የማየት ራዕይ እውን በማድረግ ሂደት አባል መሆን እና በልማት ተግባራት መሣተፍ ለሚፈልጉ አካላት ጥሪ አቅርቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.