የሕዝቡን ምርጫ እናከብራለን….
ቀደምት እናት አባቶቻችን ከግልና ከቡድን ፍላጎታቸው ይልቅ ለሀገራቸው ቅድሚያ በመስጠት የላብ፣ የደም፣ የአጥንት እና የህይወት መስዋእትነት ከፍለው ኢትዮጵያን አውርሰውናል።
እኛ የአሁኖቹ ትውልዶችም ሀገርን በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር በካርዳችን ወስነናል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ከለሊት ጀምሮ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን በምስጢር ላሻው በመስጠት የሚበጀውን መርጧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የህዝቡን ድምጽ ቆጥሮ ውጤቱን አሳውቋል፡፡ በምርጫ ያሸነፈው ለከፍተኛ ኃላፊነት ታጭቷል፡፡ በፉክክሩ በለስ ያልቀናው ለቀጣይ አምስት ዓመት ራሱን ለማዘጋጀት ሶምሶማ ይጀምራል፡፡
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የመስጠቱ ሂደቱ ከማለዳ 12:00 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም ምሽት 12:00 ድረስ ባለመጠናቀቁ ምርጫ ቦርድ መራጩ ህዝብ የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም እስከ ለሊት 6:00 አራዝሞለት ነበር፡፡
በሂደቱ ያየነው ህዝቡ ለምርጫ የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ፣ ለልማትና ለሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ነው፡፡
ህዝቡ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ዕለትና ከምርጫ በኋላ ባሳየው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ሀገር ወዳድነቱን እና የዴሞክራሲ ልምምድ ፍላጎቱን በተግባር አሳይቷል።
ህዝብ የመረጠውም አካል ይህንን የማድረግ የአምስት ዓመት ኮንትራት ውል ይወስዳል፡፡
በሂደቱ “እኔ አውቅልሃለሁ” ለሚሉት ሁሉ ህዝቡ ዛቻና ማስፈራሪያን ወደ ጎን ትቶ ድምጹን በመስጠት ያሳየው ቁርጠኝነት ሀገሩን በሰላማዊ መንገድ ለትውልድ ለማሸጋገር ያለውን መሻትና ተግባር ያሳያል፡፡
በምርጫው ህዝቡን እርጅና፣ አካል ጉዳት፣ ህመም፣ ኅዘን፣ ወሊድ፣ ሰርግ፣ ብርድ፣ ዝናብ፣ ፀሐይና ጭለማ አልበገረውም።
ይህ ሀገር የአደራና የቅብብሎሽ መሆኗን ያሳያል፡፡ የቀድሞው ትውልድ በመስዋእትነት ለእኛ ሀገር እንዳወረሰን ሁሉ፤ የአሁኑ ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማውረስ የከፈለው ዋጋ ነው፡፡
በምርጫው መራጩ ድምጹን ይወክለኛል ላለው በነፃነት ያለማንም ጫና ሰጥቷል።
በየምርጫ ጣቢያው የነበረውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢጋድ እና የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች መስክረዋል።
በምርጫ የተሳተፈው የመራጭ ቁጥር ከቁጥር በላይ ትርጉም አለው፡፡
ትርጉሙም በፍላጎት ሲሰላ ሰላም፣ የፀና ሀገረ መንግሥትና ብሔራዊ ጥቅም ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ፡፡
በሁሉም ረገድ የታፈረችና የተከበረች ሀገር መገንባት ደግሞ ዋነኛው ነው፡፡
የመራጩ ትዕግስትና ጨዋነት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ፍላጎቱ እንደሆኑ ማሳያ ናቸው፡፡
ጩኸት፣ ግርግርና የጠብመንጃ ማስፈራሪያ እንደማያስፈልገው ህዝቡ በግልጽ አቋሙን የገለጸበት ነው፡፡
ህዝቡ በምርጫ ወቅት ምንም ሳይገድበው በነቂስ ወጥቶ በጨዋነት ድምጹን ላሻው ሰጥቷል፡፡
ከምርጫ በኋላ የምርጫ ቦርድን ውጤት ሲጠብቅ ቆይቶ ቆጠራው ሲገለጽ የድካሙን ፍሬ አይቷል፡፡
አሁን ጊዜው የእኩልነትና የሀገራዊ አንድነት ነው፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን የሚከበሩበትና ሁለንተናዊ ብልፅግናችን የምናረጋግጥበት፡፡
በግል ወይም በቡድን ፍላጎትም ይሁን በተልእኮ፣ በጠብ መንጃ ሀገር ማሸበር አበቃ፡፡
የህዝቡን የምርጫ ፍላጎትና ውጤት ላየ መልእክቱ ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የጠብመንጃ ዘመን ማለፉን፡፡
የሚበጀውም የህዝቡን ምርጫ መቀበል ብቻ ነው። ህዝቡ ወስኗል፤ ኢትዮጵያም ያሻትን መርጣለች፡፡ ውጤቱንም ምርጫ ቦርድ አሳውቋል፡፡
ተመራጩ ግን የቤት ስራው ብዙ ነውና ይዘጋጅ፡፡
ኑ፤ ሀገር እንሥራ!