የነበሩ ግዳጆችን በድል ለመወጣት የህዝቡ ድጋፍ የሞራል ስንቅ ሆኖናል – ብ/ጀነራል አስፋው ማመጫ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አከናውነዋል፡፡
የመከላከያ ኢንዶክትሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል አስፋው ማመጫ ግዳጆች ሁሉ ስኬታማ እንዲሆኑ የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አያይዘውም የሃገር መከላከያ ሰራዊት ህዝቡ እያሳየው ባለው ድጋፍና አብሮነት ሰራዊቱ የበለጠ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቀጣይ ትውልድ ህልውናና ብልጽግና ሲሰራ የአረንጓዴ አሻራን ማኖር ቀዳሚ ስራ ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የካ ክፍለ ከተማ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 800 ሺህ ችግኞችን የመትከል እቅድ ያለው ሲሆን በቀጣይ ቀናት ለመትከል የታቀዱትን 300 ሺህ ችግኞች ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ለመትከል ማቀዱ ታውቋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ የሃገር መከላከያ ሰራዊት የሃገር ህልውና እንዲቀጥልና አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ደሙን ሰጥቶ መስዋዕት ሆኖ እዚህ ስላደረሰን ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሰራዊቱ የሃገርን ዳር ድንበር በማስጠበቅ፣ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ከሚከፍለው መስዋዕትነት ባለፈ እንዲህ መሰል ሃገራዊ ጥሪና ልማት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ በመሆኑም አመስግነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!