ለመከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን-የጅማ ዞን ነዋሪዎች
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር አለኝታ ለሆነው መከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የጅማ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የዞኑ 20 ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በ2ኛው ዙር 180 በሬዎችንና 40 በጎችን በድጋፍ አበርክተዋል።
የተደረገው ድጋፍም 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ነዋሪዎቹ ለሀገር አንድነትና ክብር ሌት ተቀን እየለፋ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡
የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ በበኩላቸው ÷ መከላከያ ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊት ለማስከበር የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የዞኑ ህብረተሰብ ባለው አቅም ከጎኑ መሆኑን ባደረገው ድጋፍ አሳይቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪ ÷ በቀጣይ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
በጅማ ዞን በመጀመሪያ ዙር 15 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚገመቱ 542 በሬዎች እና 408 በጎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡
በተመስገን አለባቸው
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!