Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ወግ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ወግ በዴሞክራሲ አንድ እርምጃ፣ የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ምልከታዎች በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
ውይይቱ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአቶ ሰይፈ ደርቤ፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በፕሮፌሰር ካሳሁን ፣በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በአቶ ሲሳይ ቶላና በዴስትኒ ኢትዮጵያ መሥራችና አስተባባባሪ በዶክተር ንጉሡ አክሊሉ ሀሳብ አቅራቢነት ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡
በውይይቱ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሀኑ ምርጫ ቦርድን በአዲስ መልክ ለማዋቀር፣ አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር አዋጅ በ2011 መውጣቱን፣ በሕዝብ ጥቆማ እጩዎች ቀርበው ለሥራ አስፈጻሚነት መመረጣቸው፣የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሂደቱን በቅርበት መከታተሉን፣የምርጫ ቦርድን ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም የተመለከት አዋጅ መውጣቱን አንስተዋል።
የሲዳማ ሪፈረንደም ለብሔራዊ ምርጫው መልካም ተሞክሮን ማስገኘቱን፣በቅድመ ምርጫ እስከ ክልል ድረስ ጽህፈት ቤቶች ማቋቋም፣ የምርጫ ክልል እና ጣቢያዎችን ማዘጋጀት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ፣ የታዛቢዎች ምልመላ እና ስልጠና፣ የምርጫ ቁሳቁስ ማደራጀት እና ስርጭት የመሳሰሉት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታ በተገቢው መንገድ ውሳኔ እንደተሰጠውና ሕጋዊ ያልሆኑ ተግባራት መታገዳቸውንና በምርጫው ዕለትም ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ጥረት መደረጉም ተነስቷል፡፡
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በሂደቱ የተሳተፉ ቢሆንም፣ የአውሮፓ ህብረት የታዛቢነት ውሉን ያለ አግባብ ማቋረጡን አንስተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር መድልዎ የታየበት ጫና ለማሳደር ሞክረዋል ያሉ ሲሆን ይህም ሀገር በቀል እና አህጉር አቀፍ ተቋማትን ማጠናከርና በእነርሱ ተሳትፎ የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንዳለብ አመላካች ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ካሳሁን።

ዶ/ር ንጉሡ አክሊሉ የምርጫ ቦርድ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሀን፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በምርጫው ሂደት የተጓዙበት መንገድ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል።

የፍትሕ አካላት፣ የጸጥታ አካላትና የመገናኛ ብዙሀን ገለልተኝነት ከምንጊዜውም የተሻለ መሆኑንም አንስተው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ክፍት ሆኖም ዝግ ሆኖም ምክክርና ውይይት ማካሄዳቸው ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት።

አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው ምርጫውን የማስፈጸም ሂደቱ ዋነኛ ኃላፊነት የምርጫ ቦርድ ሲሆን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ እንዲሆን መንግሥት የአጋዥነት ሚናን ተጫውቷል።

ከ37 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ ለምርጫ ተመዝግቦ ከ49 ሺህ በሚበልጡ የምርጫ ጣቢያዎች በከፍተኛ ፍላጎት የተሳተፈበት ነበር ነው ያሉት።

በቅድመ ምርጫም ልዩ ልዩ አስቻይ ማዕቀፎች ወጥተዋል፤ ምርጫ ቦርድን ያካተተ እና ከልዩ ልዩ የመንግሥት የጸጥታ እና ደህንነት አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሯል ነው ያሉት።

አቶ ሰይፈ ደርቤ ሁሉም የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ወገንተኝነታቸውን ለሙያቸው አድርገው ፓርቲ ሳይሆን ሀገር ታሸንፍ በሚል መርህ በገለልተኝነት ሠርተዋል ነው ያሉት።

የልዩ ልዩ ኃይሎችን ሀገር አፍራሽ ወሬ፣ ምርጫውን አስመልክቶ ስጋት ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎችን በማምከን በምርጫው ሂደትና በአስፈጻሚ አካላት አመኔታ አድሮበት ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሳተፍ አግዘዋል ብለዋል።

የምርጫው ዕለትም ልዩ ልዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ከጅማሬ እስከ ፍጻሜው በትጋት ዘግበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.