በክልሉ የሚከበሩ ክብረ በዓላት የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚከበሩ የብሔረሰቦች ዘመን መለወጫ እና ሌሎች ክብረ በዓላት የሕዝቦችን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፡፡
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እንዳሉት÷ በክልሉ ቀጣይ መስከረም ወር ጀምሮ የባሕል ፌስቲቫሎች፣ የተለያዩ የክልሉ ብሔረሰቦች ዘመን መለወጫና ሌሎች ታላላቅ ክብረ በዓላት በድምቀት ይከበራሉ።
የሚከበሩ የብሔረሰቦች ዘመን መለወጫ እና ሌሎች ክብረ በዓላት የሕዝቦችን አብሮነት፣ ትስስርና አንድነት ከማጠናከር ባለፈ የገቢ ምንጭ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡
የክልሉን ሕዝብ ባሕልና የቱሪስት መስህቦች በማስተዋወቅ የገቢ አቅም እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
የቢሮው ምክትልና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ በበኩላቸው ÷ በቀጣይ መስከረም ወር ጀምሮ ለሚከበሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች ዘመን መለወጫና ሌሎች ታላላቅ ክብረ በዓላት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
በክብረ በዓላቱ በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ እንደሚሳተፍ ጠቅሰው ÷ በባህላዊ ዕደ ጥበብ ውጤቶች ሽያጭና ከቱሪስቶች ከ1 ነጥብ 15 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በኢኮኖሚ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል።
የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች በክብረ በዓሉ በመታደም የክልሉን ብሔረሰቦች ድንቅ ባሕልና እሴቶች እንደሚጎበኙ ነው ያመላከቱት፡፡
የክልሉ ፀጋዎችን መሠረት ያደረጉ የቱሪዝም መስህቦችን ወደ መዳረሻነት ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የቢሮው ምክትልና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ ኑር ሳሊያ ናቸው፡፡
የቱሪዝም መስህቦችን ለመዳረሻነት ማልማት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ጠቁመው÷ መስህቦቹን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ የብሔረሰቦችን የዘመን መለወጫ በዓላት የሕዝቡን አብሮነትና አንድነት ባጠናከረ መንገድ በስኬት ለማክበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
በተካልኝ ሃይሉ