መንግስት 41 ሺህ 485 ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት 80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 41 ሺህ 485 ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ እንዲመለሱ ማድረጉን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካኝነት በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ምላሽ ማእከል ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ወገኖችን በመቀበል እና በማስተናገድ እንዲሁም ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ በማድረግ እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ገልጸዋል።
በርካታ ዜጎች በሁለቱ ሀገራት ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ አየር መንገዶች በመታገዝ መጓጓዝ ችለዋል።
ለተመላሾች ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ በማመቻቸት፣ የአልባሳት ምግብ እና የመጠጥ አቅርቦት፣ የመኝታ ፍራሽ እንዲሁም የትራንስፖርት አቅርቦት በማከናወን ረገድ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኃላፊነት የማስተባበር ስራ ሰርቷል ብለዋል አቶ ደበበ።
ከኮሚሽኑ ጋር የሰላም ሚኒስቴር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ የሴቶች እና ህፃናት ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ምላሽ ማእከል በሳምንት ሶስት ጊዜ በመገናኘት በዘጠኝ የመቀበያ ጣቢያዎች ከቦሌ ዓለም አቀፍ ጣቢያ በማምጣት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ለስደት ተመላሾቹ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደ ዓለም አቀፍ የስደት ተመላሾች ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተገልጿል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!