Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ዓመት በላይ በኮንቴነሮች ውስጥ የተከማቸ 48 ሺህ ገጀራ፣17 ሺህ መጥረቢያ እና 10 ሺህ ማጭድ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከሁለት ዓመት በላይ በኮንቴነሮች ውስጥ የተከማቸ 48 ሺህ ገጀራ፣17 ሺህ መጥረቢያ እና 10 ሺህ ማጭድ ተያዘ፡፡

መሳሪያው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ስሙ ፋና ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መያዙን ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

‹‹የተለያዩ መሣሪያዎች ፣መገልገያዎች እና አቅርቦቶች አስመጪ ድርጅት›› በሚል የንግድ ፈቃድ አማካኝነት በንግድ ስራ በሚተዳደሩት አቶ ዳርሰማ ታደሰ ህጋዊ ሂደታቸውን ሳይጠብቁ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት ቁሶች በግለሰቡ ግቢ በሚገኙ ሁለት ኮንቴነሮች ውስጥ ተከማችተው መገኘታቸው ተመላክቷል፡፡

ግለሰቡ ቁሶቹን ለማስገባት ያቀረቡትን ደብዳቤ ግብርና ሚኒስቴር ተቀብሎ ለሰላም ሚኒሰቴር የመራው ሲሆን÷ፈቃድ ሰጨው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ከሰላም ሚኒስቴር የደረሰውን የግለሰቡን ደብዳቤ ተቀብሎ ይሁንታ አልሰጠም ነበር፡፡

በዚህ መካከል ግለሰቡ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ፈቃድ ሳያገኙ በ2011 ዓ.ም 48 ሺህ ገጀራ፣ 17 ሺህ መጥረቢያ እና 10 ሺህ ማጭድ ከውጭ አስገብተው ይውላሉ ለተባለለት አላማ ሳይሰራጩ ከሁለት አመት በላይ በግቢያቸው አክማችተውት ተግኝቷል፡፡

በግለሰቡ ግቢ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ኮንቴነሮች ውስጥ ተከማችተው የተገኙት ገጀራዎች፣መጥረቢዎችና ማጭዶች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ባደረጉት ጥብቅ ክትትል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

ህጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድረግ ለህዝብ የደህንነት ስጋት የሚፈጥሩ ህገወጥ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን በማጋለጥ በኩል የህብረተሰቡ ትብብር ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተጠቁሟል፡፡

ዜጎች በቀጣይም አጠራጣሪ ሁኔታዎችን በአካባቢያቸው ሲመለከቱ ለጸጥታና መረጃ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.