የምዕራብ ጎንደር ዞን ሕዝብ ለህልውና ዘመቻው ከ85 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ሕዝብ ለህልውና ዘመቻው ከ85 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ በማድርግ ደጀንነቱን እያሳየ መሆኑን የዞኑ ድጋፍ አሰባሳቢ እና አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።
በአሸባሪው ትህነግ ተንኳሽነት እንደሀገር የገጠመውን ፈተና ለመወጣት የዞኑ ሕዝብ ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጎን በመቆም ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊና በህልውና ዘመቻው የድጋፍ አስተባባሪ አቶ ደረሰ አዱኛ ገልጸዋል።
አቶ ደረሰ እንዳሉት ለህልውና ዘመቻው እንደ ዞን ከ143 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።
ከዚህ ውስጥ 67 ነጥብ 1 ሚሊየኑ በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበ እና 18 ነጠብ 7 ሚሊየኑ በዓይነት የተሰበሰበ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድጋፉ ከነዋሪው፣ ከነጋዴው፣ ከአርሶ አደሩ፣ ከመንግሥት ሠራተኛውና ከማኅበራት መሰብሰቡን ነው አስተባባሪው የገለጹት።
የተሰበሰበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ነው ያሉት አቶ ደረሰ በዞኑ እስካሁን 210 የቀንድ ከብትና 434 በግና ፍየል በተለያዩ ግንባሮች ለሚገኘው የፀጥታ ኃይል ማስረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአዲጎሹ ግንባር ያገኘናቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶችና ህጻናት መምሪያ አማካሪና በህልውና ዘመቻው የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ ሰናይት የሽዋስ በዞኑ በዓይነት ከተሰበሰቡ ሃብቶች መካከል 886 ኩንታል ደረቅ ስንቅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከ100 ኩንታል በላይ ደረቅ ስንቅ ለፀጥታ ኃይሉ ማሰራጨታቸውንም ነግረውናል።
የአዲ ጎሹ ግንባር ሰላም አስከባሪ ኀላፊ ኮማንደር ሀገሩ አንባው የምዕራብ ጎንደር ዞን ሕዝብ ለፀጥታ ኃይሉ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድነቅ ምሥጋና አቅርበዋል።
በህልውና ዘመቻው የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ኅብረተሰቡ በወኔና በጀግንነት አለኝታነቱን እያሳየ እንደሚገኝና የሽብር ቡድኑ ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም ድጋፉ እንደሚቀጥልም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!