የኢትዮጵያ የለውጥና የልማት ጉዞ በአሸባሪው ህወሃት እኩይ ዓላማ ፈፅሞ አይደናቀፍም
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የለውጥና የልማት ጉዞ በአሸባሪው ህወሃት እኩይ ዓላማ ፈፅሞ እንደማይደናቀፍ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ ገለጹ።
በአዋሽ አርባ የውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ለሚሰለጥኑ ምልምል ወታደሮች የአየር ሃይል የኪነ-ጥበብ ቡድን አባላት የተለያዩ ዝግጅቶችን አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ፥ “የኢትዮጵያ የለውጥና የልማት ጉዞ በአሸባሪው ህወሃት እኩይ ዓላማ ፈፅሞ አይደናቀፍም” ብለዋል።
አሸባሪው ህውሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ የተለያዩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም የሽብር ቡድኑ ዓላማ በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊትና አገር ወዳድ ዜጎች የጋራ ትብብር እየከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ በየትኛውም የጥፋት ሃይል የማትፈርስ ታላቅ አገር መሆኗን በጋራ ከንዳችን እናረጋግጣለን” ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የአዋሽ አርባ የውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ተመስገን አቦሴ፥ “ለአገር ህልውና ዘመቻው ሁሉም፣ መቼም፣ በየትም በመዝመት የአገር አለኝታነቱን እያሳየ ነው” ብለዋል።
አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ሁሉም በየመስኩ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው፥ “የአየር ሃይል የኪነ-ጥበብ ቡድን ዛሬ እያደረገ ያለውም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።
የኪነ ጥበብ ቡድኑ አባላት የሰራዊቱን ሞራልና ስነ-ልቦና ለማነቃቃት በመገኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
“ኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ውርሳችን ነው” ያሉት ሜጀር ጀነራል ተመስገን፥ የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት ቁርጠኛ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሁላችንም ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸው ፥የአሸባሪውን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ የኢትዮጵያን ልማትና እድገት እንደሚያስቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!