Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ ልዑክ ከተመራው የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ ልዑክ አምባሳደር ባርሊ ሻሮን ከተመራው የእስራኤል ከፍተኛ የመንግስት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ ÷ሁለቱ ሀገራት በመከባበርና እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በማውሳት ይህንን ምቹ ሁኔታ በሀገራቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀም አንደሚያስፈለግ ጠቁመዋል።

በግብርና ምርታማነት፣ አቅም ግንባታ፣ በሰላም እና ደህንነት ዘርፎች የጋራ ትብብሮች እንዲጠናከሩ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት የገለፁት አቶ ደመቀ የኢትዮጵያን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ አዲስ መንግስት መመስረቱን አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ በተጻረረ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት እስራኤል ድጋፍ እንድትሰጥ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸው ÷በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡

አምባሳደር ባርሊ ሻሮን በበኩላቸው÷ ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው መረጃውን ለእስራኤል መንግስት እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል፡፡

እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አጠናክራ እንደምታስቀጥልም ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.