በአዲስ አበባ የጎርፍ መከላከልና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በቀጣይ የክረምት ወራት የሚተገበር የጎርፍ መከላከልና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ ተጀምሯል።
ንቅናቄውን ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ÷ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ የመዲናዋ አካባቢዎች ጎርፍን የመከላከል ስራ በንቅናቄ ይከናወናል ብለዋል።
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በአቃቂ ቃሊቲ የጎርፍ ተጋላጭነት ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
የጎርፍ መከላከልና የአደጋ ዝግጁነትን መሠረት አድርጎ በተከናወኑ ተግባራት ተጋላጭነትን እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
አደጋ ቀድሞ የመከላከል ዝግጁነት ስራዎች የንቅናቄው አንድ አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪ ተቋማት በክፍለ ከተሞች መገንባታቸው አደጋ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ማስቻሉን ገልጸዋል።
ወንዞች ንፁህ ውሃ ይዘው የሚወርዱ እንጂ አደጋ የሚያደርሱ እንዳይሆኑ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ወንዞችን ወደ ተፈጥሯዊ ይዞታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የውሃ መፋሰሻ ዲቾች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የአዲስ አበባ የላይኛውን ተፋሰስ አካባቢ መልሶ በማልማት በተሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ይህም እንደ አቃቂ ቃሊቲ ባሉ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች ይደርሱ የነበሩ አደጋዎችን ለመቀነስ አስችሏል ብለዋል።
ይህንን አልፎ ለሚከሰቱ አደጋዎች በክፍለ ከተሞች በተገነቡ የአደጋ መከላከል ተቋማት ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በእዮናዳብ አንዱአለም