ከመቼውም ጊዜ በላይ ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠት ወሳኝ ነው – አቶ አባ ዱላ ገመዳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመቼውም ጊዜ በላይ ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠት ወሳኝ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳሲ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ተናገሩ።
በዛሬው ዕለት በጅማ ዞን ሸቤ ሶምቦ ወረዳ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
የኦሮሚያ ልማት ማህበር በ10 ሚሊየን ብር በጀት የሚገነባው ትምህርት ቤቱ ግንባታም በ40 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሏል።
በዚህ ወቀት የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢና የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራች አቶ አባ ዱላ ገመዳ ÷ሀገር በመለወጥ ሂደት ውስጥ የተማረ የሰው ሃይል ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ልማት ማህበርም ተወዳዳሪ ተማሪዎች ለማፍራት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ክልል በ2013 የትምህርት ዘመን ጅማ ዞን ብዙ ተማሪዎችን ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት በማስገንባት ቀዳሚ ነበር ያሉ ሲሆን÷ ማህበሩ ከ10 ሚሊየን ብር የማስገንቢያ ገንዘብ በተጨማሪ የኮምፒውተርና መጽሐፍ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ ÷የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ትምህርት ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረው እንደ ክልል ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎቹ በ5 ነጥብ 3ሚሊየን ብር ወጪ የተሰራ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመረቁ ሲሆን÷ በኪሼ ቀበሌ በ2 ሺህ 286 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለ የሩዝ ምርትም ጎብኝተዋል።
በዝግጅቱ ላይ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፣ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፣ አቶ ደጀኔ ኢቲቻና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና ክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
በተመስገን አለባቸው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!