በሰሞኑ ወታደራዊ ኦፕሬሽን የተደናገጠው ህወሓት የጎረቤት ሀገራት ተቃዋሚዎችን ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ውስጥ መግባቱን የፋና ምንጮች ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በተካሄደው ወታደራዊ ኦፕሬሽን የተደናገጠው ህወሓት የጎረቤት ሀገራት ተቃዋሚ የሆኑና ደጋፊዎቹ ሊሆኑ የሚችሉ ኃይሎችን ድጋፍ የመጠየቅ ስራ ውስጥ መግባቱን ፋና ከታማኝ ምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት ጎረቤት ሀገራት በስደተኛነት ያከማቻቸውን አባላቱን በመጠቀም ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን አንዳንድ ኃይሎች ጋር ለመምከር መሞከሩን ምንጫችን ጠቁመውናል።
በሱዳን በስደተኝነት የሚኖረው ጄኔራል ፍሥሐ የተባለ ሰው የሳምሪን ስኳድ እያሠለጠነ ይገኛል። ሳምሪ በሱዳን ሠልጥኖ ወደ ምዕራብ ጎንደር እንዲገባ የተዘጋጀ የሽብር ቡድን ሲሆን፥ ዓላማውሞ ንጹሐንን መግደልና ሽብር መንዛት ሲሆን፥ እስካሁን በተደጋጋሚ ሞክሮ ድንበር አልፎ መግባት ግን እንዳልተሳካለት ምንጫችን ይጠቁማል፡፡
ከሰሞኑ የህወሓቱ የሽብር ቡድን መሪ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሰዎችና ጀነራል ፍሥሐ የተባለ ግለሰብ ከአንዳንድ የሱዳን ባለሥልጣናት ጋር መክረው ነበር ብሎናል ታማኝ ምንጫችን።
ምክክራቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን ጥቃት ለመቀልበስ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማግኘት ያሰበ መሆኑ ነው የተመለከተው።
የሱዳን ሰዎች እነ ደብረ ጽዮን የጠየቁትን ሙሉ በሙሉ ለማሟላት እንደማይችሉና ከግብጽ ጭምር ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚሞከር ቃል ገብተዋል ይላል ታማኝ ምንጫችን።
በተያያዘም የደቡብ ሱዳኑ የሪክ ማቻር ሰዎች የሕወሓት ሰዎችን ለማስታጠቅና ወደ ጋምቤላ ለማስገባት በጁባ እንደመከረም ተደርሶበታል፡፡
በደቡብ ሱዳን ጉዳይ አንዳንድ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳሉበት ምንጮች ገልፀዋል።
በዚሁ ባገኘነው መረጃ ዙሪያ ያናገርናቸው በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒተ ሞርጋን እንደ ደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ነው የምንፈልገው ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ የህወሓት የሽብር ቡድን ከሳልቫኪር ማየርዲት መንግስት ጋር ግንኙነት እንደሌለው፤ መንግስታቸውም የኢትዮጵያን ሰላምና ብልፅግና የሚሻ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
እንደምንጫችን ከሪክ ማቻር ቡድን ጋር ለህወሓት የሚሰራው እና ዋና አቀናባሪው የስዬ አብርሃ ወንድም አሰፋ አብርሃ ሲሆን፥ ወደ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለደቡብ ሱዳን ባለ ሥልጣናት ለጊዜው ለመስጠት መታሰቡ ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒተ ሞርጋን ሪክ ማቻር የት እንዳለም አናውቅም ብለዋል።
የጋምቤላ አማፂያን ከሪክ ማቻር ኃይል ጋር ግንኙነት እንዳለውና ህወሃትም ይህንን አጋጣሚ ሊጠቀም እንደሚችል ግን እናስባለን ነው ያሉት፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት ግን ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም ነው ያሉት፡፡
በተቃራኒው ግን ሪክ ማቻር ህወሃት በስልጣን ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ግንኙነት እንደነበረውና አዲስ አበባ ላይም መኖሪያ ተሰጥቶት ይኖር እንደነበር እናውቃለን ብለዋል፡፡
ሪክ ማቻርም ሆነ ህወሓት ቀድሞ የነበራቸውን ግንኙነት በማደስ አሁን ለጋራ አላማቸው አብረው ሊሰሩ ይችሉ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲኖራት እንፈልጋለን ያሉት አምባሳደሩ፥ ስለዚህም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን እንድትጎናፀፍ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና የተወጣች ሀገር መሆኗን በፍፁም አንረሳም ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ጭምር ሰጥታ ተጠቃሚ እያደረገችን ትገኛለች ነው ያሉት አምባሳደር ጀምስ ፒተ ሞርጋን። እንደ መንግስት ይህንን ውለታ ረስተን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ማናቸዉንም ድርጊት አንፈፅምም ብለዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም ገልፀዋል።
ሰላሟም ተጠብቆ ጠንካራ አፍሪካዊት ጎረቤት ሀገር እንድትሆን እንመኛለን፤ ለዚህም ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ የሱዳን ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ጣልቃገብነት እና ከህወሓት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጥራት በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደርን ለማናገር የሞከርን ሲሆን፥ “በቀጣይ ቀናት ማብራሪያ እሰጣለሁ፤ አሁን አይመቸኝም” የሚል መልስ ሰጥተውናል፡፡