ባለፉት 3 ዓመታት ከዳያስፖራው 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ቤት ተልኳል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 3 ዓመታትም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ወደ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ቤት መላክ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሃብት የማሰባሰብ ንቅናቄን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ውይይት ከሚመለከታቸው ዲፕሎማቶችና የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮች ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ከዚህ በፊት በነበረው ጊዜ በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡና በሀገራቸው ጉዳዮች ተሳታፊ እንዳይሆኑ ገደብ ተጥሎባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
በሀገራችን ከመጣው ለውጥ በኃላ ግን ለዳያስፖራ ማህበረሰብ አዲስ አይነት የተሳትፎ በሮችንና የሀገር ባለቤትነት ዕድልን እንደተፈጠረለት ነው የገለጹት።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ወደ 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ቤት የተላከ ሲሆን÷ ይህም በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራቱንም ጠቁመዋል።
ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራት አንጻርም በውጤት የታጀቡ በርካታ እንቅስቃሴዎች መከናወናቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን÷መንግስትም ዳያስፖራው ሊያበረክት የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን በማቋቋም ተቋማዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዳያስፖራው አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና በመቃወም፣ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ትግሉም እነዚህ ሀይሎችና ሚዲያዎቻቸው የሚያናፍሱትን የሀሰት መረጃ በማጋለጥ ባደረገው የተጠናከረ እንቅስቃሴ ትግሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ብሎም የሁሉም ነጻነት ናፋቂ ህዝቦች አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ የተዘጋጀውን መተግበሪያ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተደረገው ከፍተኛ ድጋፍም ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዘመቻውን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎም ዳያስፖራው በቡድንና በተናጠል የግል ኑሮውን በመተው በአካል የትግሉን ጎራ በመቀላቀል ለሀገሩ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አንድ ሚሊየን ዳያስፖራ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ የቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ በከፍተኛ ቁጥር እንዲመጣ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን የሚያስተባብር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ብሄራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ በይፋ ስራ መጀመሩንም አብስረዋል።
በሀገራችን ላይ የሚደረገው ጫና ቀጣይ ሊሆን እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ዳያስፖራው እያከናወነ ያለውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሃብት የማሰባሰብ ህዝባዊ ንቅናቄዎች አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጥሪ አቅረበዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!