እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት ያልተገባ የሰብዓዊ መብት አያያዝ አልታየም – ኢሰመኮ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት ያልተገባ የሰብዓዊ መብት አያያዝ አልተመለከትሁም አለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)።
በኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የተመራ የኮሚሽኑ ቡድን በአርባምንጭና በጅማ ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን ተመልክቷል፡፡
በዚህ ወቅት ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እንዳሉት÷ ለአካል ጉዳተኞች ጭምር የተመቻቹ የምርጫ ጣቢያዎች ተመልክተዋል።
የምርጫ መስፈርቶችን ያሟላ የምርጫ ሂደትን መታዘባቸውንም ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊና መስተጓጉል ያልታዩበት መሆኑን ጠቅሰው፥ ቡድኑ እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት ያልተገባ የሰብዓዊ መብት አያያዝ አለመመልከቱን ገልጸዋል።
የምርጫ ታዛቢዎች እና መራጩ ዜጋ በሰዓቱ በምርጫ ጣቢያው በመገኘት ምርጫውን ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በ175 የምርጫ ክልሎችና ከ2 ሺህ 700 በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች የመታዘብ ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በምርጫ ሂደቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በመከታተልና በድህረ ምርጫ የሚኖረውንም ሂደት በአግባቡ በመምራት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በምርጫ ሂደቱ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ በተዘጋጀው የቅሬታ መከታተያ ስርዓትም የምርጫውን ሂደት እየተከታተለ እንደሆነ አስረድተዋል።
ምርጫው ሕብረተሰቡ ለቀጣይ አምስት አመታት የሚመራውን አካል በድምጹ የሚያረጋግጥበት በመሆኑ እንደሀገር ለመምረጥ የተመዘገበው ከ54 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በመምረጥ ሕገመንግስታዊ መብቱን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
#ኢትዮጵያ #ኢትዮጵያእየመረጠችነው #በምርጫብቻ #ፋናዲጂታል #Election #fanadigital #Ethiopia #Ethiopiavotes #Democracy #fanatelevision