Fana: At a Speed of Life!

በማክሮ ኢኮኖሚው በተወሰደው እርምጃ ለውጥ ተመዝግቧል- መንግስት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚው ለመገንባት በተወሰደው እርምጃ ለውጥ መመዝገቡን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ የማክሮ ኢኮኖሚውን አፈፃፀም ለማሻሻል በተወሰዱ እርምጃዎች ለውጥ መመዝገቡን ገልፀዋል።
ለአብነትም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በተወሰዱ እርምጃዎች ካለፉት ሁለት ወራት ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ በማሳየት 33 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ነው ያመለከቱት።
የምግብ ነክ ሸቀጦች ግሽበት ካለፈው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ1 ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንም ጠቁመዋል።
የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በዚህም ወጪን የመቀነስ እርምጃዎችና እና አስተዳደራዊ ለውጦች በመደረጋቸው በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
እነዚህ የተከናወኑ ስራዎችም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር የሚያስችሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል ነው ያሉት፡፡
በ2014 በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ውስጥ የፌዴራል መንግስት የታክስ ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ10 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷልም ብለዋል፡፡
በተጠቀሱት ወራት የፌደራል መንግስት አጠቃላይ ወጪ ደግሞ በ22 ነጥብ 7 በመቶ መጨመሩን ነው ያመለከቱት፡፡
ለዚህም የመደበኛ ወጪ 34 በመቶ መጨመር እና የካፒታል ወጪ በ4 በመቶ መጨመር በምክንያትንት ተጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ ባለፉት 3 ወራት የሸቀጣ ሸቀጦች የወጪ ንግድ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ16 በመቶ
አካባቢ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት።
በዚህም ለሀገሪቱ 972 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ገቢ ማስገኘት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ ከሚገኙት የወጪ ንግድ የገቢ ማስገኛ ምርቶች ውስጥ ቡና ዋነኛው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ቡና ከጠቅላላ የሸቀጦች ወጪ ንግድ ገቢ ላይ የ33 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጪ የተላከው የቡና ምርት ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃጸርም የ61 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡

ከቡናው ዘርፍ በወጪ ንግድ የተገኘው አጠቃላይ ገቢም 329 ሚሊን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ጭማሪ ማሳየቱን ነው ያብራሩት፡፡

በቀጣይም የአገር ውስጥ ምርትን መጨመር፣ የሸቀጦችን አቅርቦት የማሻሻል እና በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚስተዋሉ አሻጥሮችን መቆጣጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች በዋጋ የማይተመነውን የሰው ህይወት ጨምሮ ዘርፈ ብዙ የሆኑ እጅግ ከፍተኛ ጉዳትና ውድመት ማድረሱን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
የሽብር ቡድኑ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን ጨምሮ ለዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት ላይ ውድመት አድርሷል ብለዋል፡፡
አሁንም ነፃ በሚወጡ አካባቢዎች ሁሉ ወደ ፊት በጥናት ተደግፎ የሚቀርቡ መረጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፥ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የመልሶ ማቋቋም ሥራው ብዙ ቢሊየን ብር ያስፈልገዋልም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው፡፡
የመልሶ ማቋቋም ሥራው በፍጥነት መካሄድ እንዳለበት ጠቁመው፥ ለዚህም ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለት አሳስበዋል፡፡
የመልሶ ማቋቋም ሥራውን መንግሥት በሚያደርገው ጥረት ብቻ በሚፈለገው ፍጥነት ማሳካት ስለማይቻል፥ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት ተረድቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.