Fana: At a Speed of Life!

በደሴና ኮምቦልቻ የጤና መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው በህወሃት ወድመዋል – የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ወጪ ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የደሴና የኮምቦልቻ ጤና ተቋማት በአሸባሪውና ወራሪው የህውሓት ቡድን አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነው መውደማቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሸባሪውቡድን አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኖ የወደመ ሲሆን ÷ ቡድኑ በተደራጀ መልኩ የህክምና መሳሪያዎችንና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ጭኖ ከመውሰዱ ባለፈ የቀሩትንም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጎ ሙሉ በሙሉ ማውደሙን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ከእነዚህም መካከል በተኝቶ ህክምና፣ በፅኑ ህክምናና በአንስተኛና በከፍተኛ የቀዶ ህክምና ክፍሎች የነበሩ በብዙ ሚሊየን ብር የተገዙ የትንፋሽ መስጫ (ቬንቲሌተር) እና አንስቴዥያ ማሽኖች ወስዷልም ነው ያለው፡፡

ቀሪዎቹም ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት በማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ80 ዓመት ታሪክ ያለውና ለትግራይና ለአፋር አጎራባች ክልሎች ጭምር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፥ በዓመት ከ450 ሺህ ህዝብ በላይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል ውድመትና ወረራ እንደተፈጸመበት ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ 200 አልጋ የነበረው ሲሆን ÷ በቅርቡ በቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እና በጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ነው፡፡

በተጨማሪም ከመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቅርንጫፎች መካከል አንዱ የሆነው የደሴ ቅርንጫፍ በሽብርተኛው እና ወራሪው የህወሓት ቡድን ከፍተኛ ዝርፊያ እና ጉዳት ደርሶበታል፡፡

የጥፋት ቡድኑ በክምችት የነበሩ መድኃኒቶችን እና ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን የቻለውን በመዝረፍ እንዲሁም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡

ቅርንጫፉ ለ27 ሆስፒታሎች፣ ለ303 ጤና ጣቢያዎች፣ ለ60 ወረዳዎች እንዲሁም ከህግ ማስከበር ዘመቻው እስከ የህልውና ዘመቻው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የመድኃኒት እና ሌሎች የህክምና ግብዓት በማቅረብ አገልግሎት ሲሰጥ ነበረ፡፡

በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የተገነባ ግዙፍ የእናቶች እና የህፃናት ክትባት ግብዓት ማከማቻ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዘን፣ ዋና ማጋዘን፣ ቢሮዎች፣ የማከማቻ መሰረተ ልማት፣ ፎርክሊፍቶች ፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ስርዓቶችን፣ የቢሮ መሳሪያዎች እና ሌሎች ንብረቶችን ማውደሙን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም ቡድን ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታልን የጦር ማዘዣ በማድረግ ሙሉ በሙሉ መዝረፉንና ማውደሙን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገልጿል።

የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል በ1947 ዓ.ም የተቋቋመ እና ለ67 ተከታታይ ዓመታት ለሕዝብ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አሚኮ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.