መንግስት በውስጥና በውጭ ካለው ህዝብ ጋር በመሆን የሚካሄድበትን የውጭ ጫና የመመከት ስራውን እየሰራ ነው- አምባሳደር ሬድዋን
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መንግስት በውስጥ እና በውጭ ካለው ህዝብ ጋር በመተባበር በማስረጃዎች ላይ ተመሰርቶ በተቀናጀ መልኩ የሚካሄደውን ጫና የመመከት ስራ እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።
አምባሳደር ሬድዋን ቲቪ ጄ ከተሰኘ የጀማይካ ቴሌቪዥን ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
በቀጥታ ስርጭት በተላለፈው ቃለ ምልልስ አሁን በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ቀውስ መነሻው የህወሓት የለውጥ እምቢተኝነት እንደሆነ አስረድተዋል።
አሸባሪው ኃይል የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው አሰቃቂ ጥቃት ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በቃለ ምልልሱ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉት ሙከራ በተጨባጭ የሚታይ እንደሆነ አመልክተዋል።
አሸባሪውን ኃይል በመደገፍ የሚዲያ ኘሮፖጋንዳን በመክፈት፣ ዲኘሎማሲያዊ እና ፓለቲካዊ ጫናን በመንግስት ላይ በመፍጠር የተደረጉ ዘመቻዎችን አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል፡፡
በተራዕዶ ስም የተሰማሩ ተቋማት አሸባሪውን ኃይል ሲደግፉ መያዛቸውን፣ በትግራይ “የዘር ማጥፋት” ተፈፅሟል የሚል ሃሰተኛ ትርክት ለመፍጠር የተቀናጀ ርብርብ መደረጉን፣ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን ለመጉዳት በተደጋጋሚ ረቂቅ ውሳኔ መዘጋጀቱን አምባሳደሩ እንደማሳያ ጠቅሰዋል።
እነዚህ አካላት የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርጋቸውን የሰላም እና ሌሎች በጎ ጥረቶች እንዳላዩ በማለፍ ጫና የመፍጠር ሙከራው እንዳልተቋረጠም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።
አለምአቀፍ ማህበረሰቡ ኢትዮጵያን ለቆ እንዲወጣ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ ሊካሄዱ የታቀዱ ጉባኤዎች ወደ ሌሎች ሃገራት እንዲዛወሩ የሚደረጉ ግፊቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን÷ መንግስት በውስጥ እና በውጭ ካለው ህዝብ ጋር በመተባበር በማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ በተቀናጀ መልኩ የሚካሄደውን ጫና የመመከት ስራን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግስት ለውይይት ዝግጁ መሆኑን እና ሃገሪቱም የውስጥ ችግሯን በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት አምባሳደር ሬድዋን በቃለ ምልልሳቸው ላይ ማስገንዘባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በጀማይካ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል የሆኑት ዮዲት ጌታቸው ሃይልተን በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን÷ በጀማይካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከራስ ተፈሪ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመተባበር በኪንግስተን ከተማ ስኬታማ የሆነ የበቃ ተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!