በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ልማት ለዘማች ቤተሰቦች እገዛ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ልማት ህብረተሰቡን በማስተባበር ለዘማች ቤተሰቦች እገዛ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
እስካሁን ባለው የበጋ ወቅት የዘማች ቤተሰቦች ይዞታ የሆነ 1 ሺህ ሄክታር ማሳ በተለያዩ የውሀ አማራጮችና በቀሪ እርጥበት በልዩ ልዩ ሰብሎችና በጓሮ አትክልት እየለማ መሆኑ ተመላክቷል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ ሃውልቱ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ በመደበኛው የመስኖ ልማት 20 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር የመሸፈን ስራ ተጀምሯል።
እስካሁን ባለው የበጋ ወቅት በ15 ወረዳዎች ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች 500 ሄክታር መሬት በተለያዩ የውሀ አማራጮችና 500 ሄክታር መሬት ደግሞ በቀሪ እርጥበት በልዩ ልዩ ሰብሎችና በጓሮ አትክልቶች እየለማ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡
ለዘማች ቤተሰቦቹ በህብረተሰብ የጉልበት እገዛ በቀሪ እርጥበት ጓያ፣ ሽምብራና ስንዴ እንዲሁም የተለያዩ የውሀ አማራጮችን በመጠቀም ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያና ሰላጣ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የህልውና ዘመቻው አካል የሆነውን የግብርና ስራን ውጤታማ ለማድረግ በዘንድሮ የበጋ ወራት 20 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ እስካሁን 13 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ተናግረዋል።
በልማቱ እየተሳተፉ ላሉ አርሶ አደሮች ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም ገልጸዋል ።
እንደ አቶ ሀውልቱ ገለጻ 28 የውሃ መሳቢያ ሞተሮችም በብድርና እጅ በእጅ ሽያጭ ተሰራጭተው አገልግሎት እየሰጡ ነው።
በዞኑ በበጋ መስኖ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!