የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሀይቅን ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም ሀላፊነት መውሰዱን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 4 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በአሸባሪ ቡድኑ ህወሓት ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ የተፈፀመበትን የሀይቅ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም ሀላፊነት መውሰዱን አስታወቀ።
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሀይቅ ሆስፒታልን መልሶ ለማቋቋም ሃላፊነት መውሰዱን አስታውቀዋል።
ስራ አስኪያጁ “እመኑኝ ከዚህ በኋላ ስለደረሰው ጥፋት ብቻ አናወራም ስለምናመጣው ልማት እንጂ” ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
የጤና ሚኒስቴር ህወሓት ወርሮ በያዛቸው የአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ የጤና መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ እንዳወደማቸው መግለጹ ይታወሳል።
ለአብነትም የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሸባሪውቡድን አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኖ የወደመ ሲሆን ÷ ቡድኑ በተደራጀ መልኩ የህክምና መሳሪያዎችንና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ጭኖ ከመውሰዱ ባለፈ የቀሩትንም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጎ ሙሉ በሙሉ ማውደሙንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ከእነዚህ መካከል በተኝቶ ህክምና፣ በፅኑ ህክምናና በአነስተኛና በከፍተኛ የቀዶ ህክምና ክፍሎች የነበሩ በብዙ ሚሊየን ብር የተገዙ የትንፋሽ መስጫ (ቬንቲሌተር) እና አንስቴዥያ ማሽኖች ወስዷልም ነው ያለው፡፡
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ80 ዓመት ታሪክ ያለውና ለትግራይና ለአፋር አጎራባች ክልሎች ጭምር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፥ በዓመት ከ450 ሺህ ህዝብ በላይ አገልግሎት ሲሰጥጭ ቆይቷል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል ውድመትና ወረራ እንደተፈጸመበት ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ሆስፒታሉ 200 አልጋ የነበረው ሲሆን ÷ በቅርቡ በቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እና በጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ነው፡፡
በተጨማሪም ከመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቅርንጫፎች መካከል አንዱ የሆነው የደሴ ቅርንጫፍ በሽብርተኛው እና ወራሪው የህወሓት ቡድን ከፍተኛ ዝርፊያ እና ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ቅርንጫፉ ለ27 ሆስፒታሎች፣ ለ303 ጤና ጣቢያዎች፣ ለ60 ወረዳዎች እንዲሁም ከህግ ማስከበር ዘመቻው እስከ የህልውና ዘመቻው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የመድኃኒት እና ሌሎች የህክምና ግብዓት በማቅረብ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር፡፡
በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የተገነባ ግዙፍ የእናቶች እና የህፃናት ክትባት ግብዓት ማከማቻ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዘን፣ ዋና ማጋዘን፣ ቢሮዎች፣ የማከማቻ መሰረተ ልማት፣ ፎርክሊፍቶች ፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ስርዓቶችን፣ የቢሮ መሳሪያዎች እና ሌሎች ንብረቶችን ማውደሙን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም ቡድን ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታልን የጦር ማዘዣ በማድረግ ሙሉ በሙሉ መዝረፉንና ማውደሙን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገልጿል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!