በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አተገባበር ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አተገባበር መመሪያ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በትግብራ ላይ ያለው መመሪያ ላይ ማሻሻያ ማድረግ በማስፈለጉ በተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መግጠም ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ መወሰኑን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ከሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ የማስገጠምና በተቀመጠው ደረጃ መሰረት መገጠሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ነበረባቸው፡፡
የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያው ሊገጠምባቸው የሚገባቸው ተሽከርካሪዎች ዓይነትና ተያያዥ ችግሮችን በጥናት በመለየት ምላሽ መስጠት በማስፈለጉ በፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ አተገባበር ላይ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
በአተገባበሩ ላይ እየታየ ያለውን ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፈተሸ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።
እስከዚያው ድረስ ግን አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ባለንብረቶች በማንኛውም ጊዜ መግጠም እንዳለባቸው አውቀው፤ የግዴታ ስምምነቱን እየፈረሙና አስፈላጊ ሰነዶቻቸውን በአባሪነት በማያያዝ በተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መግጠም ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡