Fana: At a Speed of Life!

በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት እቅዶችን በማሳካት ብልፅግናን እናረጋግጣለን – አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ)  በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት እቅዶችን በማሳካት የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና እናረጋግጣለን አሉ የሶማሌ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ።

ርዕሠ መስተዳድሩ ክልሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በጋራ በሚሰራቸው ስራዎች ላይ ከተቋሙ የስራ ኃላፊዎች  ጋር ዛሬ በጅግጅጋ መክረዋል::

አቶ ሙስጠፌ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፥  የሚገጥሙንን ማናቸውንም ፈተናዎች እንደ ሀገር በሁሉም ግንባሮች በአሸናፊነት በመወጣት የኢትዮጵያን ህልውና በማረጋገጥ ገናና ስሟን በአለም መድረክ እናሰርፃለን ብለዋል::

በአሸባሪው ህወሃት  ላይ የተገኙ ድሎችን በማሻገር የሀገር ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።

በክልሉ የተጀመሩ የከተማ፣  የመስኖ፣  የአርብቶ አደር እና የውሀ ልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ከዳር ለማድረስ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው ብለዋል ርዕሠ መስተዳድሩ።

የህዝብ አጀንዳዎችን በማንሳት መስራት ደግሞ ግንባር ቀደሙ የሚዲያ ድርሻ መሆኑን አንስተዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ደግሞ ካለው ሰፊ ተደራሽነት እና አድማጭ ተከታይ አንፃር ለክልሉ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ተልዕኮውን ሊወጣ ይገባዋል ነው ያሉት።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፥ እንደ ሀገር የተከፈተብንን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ እና እውነታውን ለአለም በማሳየት ለህዝባችን አለኝታ እንሆናለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

ለህዝባዊ አጀንዳዎች ትኩረት በመስጠት  ከክልሉ መንግስት ጋር በትብብር እንሰራለንም ብለዋል።

አቶ አድማሱ ባለፉት ሶስት አመታት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አመርቂ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው፥ ይህንን መልካም ተምክሮ ለማስፋት መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ በኩል ፋና የድርሻውን እንደሚወጣ ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.