የፌደራል ፖሊስና ኢትዮ ቴሌኮም በአማራ ክልል የወደሙ ተቋማትን ለማቋቋም የሚውሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ኢትዮ-ቴሌኮም በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ 178 ፖሊስ ጣቢያዎችን እና አምስት የዞን ፖሊስ መምሪያዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ10 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ለቢሮ ግብአት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ።
በድጋፍ እርክክቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ እና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ መገኘታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ፖሊስ ጣቢያዎቻችንን ለሰላማችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላላቸው የወደሙትን መልሰን በመገንባት እና የፀጥታ ስራዎቻችን የበለጠ ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ወንበር፣ ኮምፒውተርና ፕሪንተር የመሳሰሉ ድጋፎችን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከድጋፍ ጎን ለጎን ነፃ በወጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመጠገን የስልክ አገልግሎት በፍጥነት እንዲጀመር እያደረገ መሆኑን ተናረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው÷ አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ንፁሃንን በመግደል እንዲሁም ንብረታቸውን በመዝረፍና በማውደም አሰቃቂ በደሎችን መፈፀሙን ገልጸው÷ ፖሊስ አሸባሪ ቡድኑ የፈፀመውን ግፍ በመመርመር ለፍትህ አደባባይ እንዲያቀርብልን እንፈልጋለን ሲሉም ጠይቀዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የመንግስት ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ አውድሟል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በክልሉ በ5 ዞኖች ብቻ 83 የሚደርሱ የፖሊስ ጣቢያዎች በሽብር ቡድኑ መውደማቸውን ጠቁመው÷ የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!