Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል በዓልን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓልን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ህዝብን በሚጎዳ መልኩ ዋጋ ይጨምራሉ ያሉት የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ፥ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የህልውና ትግል ላይ በህብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አሸባሪውን ከመደገፍና ከአገር ክህደት አይተናነስምና የክልሉ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ለገና በዓል በክልሉ የዘይትና የስኳር አቅርቦት የተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው፥ አቅርቦቱ ግን ቀድሞ ከነበረው 50 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህም ከውጭ አቅርቦቱን ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ የተከሰተ መሆኑን ገልጸው፥ ይህን መሰረታዊ ፍጆታ ያለአግባብ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ አከፋፋዮችና ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

50 በመቶ በመቅረቡ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ አያስቸግርም ወይ ብሎ ፋና ላቀረበው ጥያቄ፥ ማህበረሰቡ ቀድሞ ይወስድ ከነበረው ኮታ መጠኑ ተቀንሶ እንደሚሰጥ ገልጸው ፤ ሆኖም እንደሚዳረስ አንስተዋል።

በክልሉ ከተመን በላይ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ይታያል ያሉት አቶ ማሄ ቦዳ፥ አንዳንድ የማደያ ባለቤቶች በህጋዊ መንገድ ካለመሸጣቸው በተጨማሪ ‘ቀን ነዳጅ የለም’ እያሉ ማታ ማታ ደግሞ በጭማሪ ሲሸጡ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

ይህን ለመቆጣጠር መንግስት ባስቀመጠው ዋጋ በማይሸጡ ማደያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም አንስተዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በዓድ ነገርን በምርት ላይ የሚጨምሩ አካላትም ከዚህ እኩይ ተግባር እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ሃላፊው፥ ከዚህ በፊት ባዕድ ነገር ቀላቅለው የተገኙ 3 ሺህ 500 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡

90 ኩንታል በርበሬ ከባዕድ ነገር ቀላቅለው የተገኙ አካላትን እንማሳያ አንስተው፥ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት መወሰዱን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጥሪ በመቀበል ወደ አገር ቤት እየመጡ ባሉት ዳያስፖራዎች በሚጠቀሙት አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ነው ያሉት ሃላፊው፥ ልጆቻችንን በአክብሮትና በተመጣጣኝ ዋጋ ልናስተናግዳቸው ይገባል ብለዋል።

በጥላሁን ይልማ

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.