የሐረር ከተማና አካባቢውን የኃይል እጥረት የሚቀርፍ ስራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማና አካባቢው የነበረውን የኃይል እጥረት ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ ስራ መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያ ኦፕሬሽን የምስራቅ ሪጅን አስታወቀ።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንዳስታወቁት፥ ያለፉት ሁለት ዓመታት የሐረር ከተማና አካባቢው ከፍተኛ የኃይል እጥረት አጋጥሞት የነበረ ሲሆን፥ ችግሩን ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ጊዜያዊና ቋሚ መፍትሄዎች እየተነደፉ ሲተገበሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጋሻው ገለፃ የኃይል እጥረቱ ብቸኛ መንስኤ የፓወር ትራንስፎርመሮች ከአቅም በላይ የኃይል ጭነት በመሸከማቸው ነው።
ይህንንም ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር የሆነ ትራንስፎርመር ግዢ ተፈፅሞ ትራንስፎርመሩ ሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ያለምንም ችግር እንዲቀመጥ ተደርጓል ብለዋል።
የፓወር ትራንስፎርመሩን ተከላ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን የገለፁት አቶ ጋሻው ተከላው ሲጠናቀቅ የሐረሪ ብሔራዊ ክልል ከተሞችንና እንደ አወዳይ እና ኮምቦልቻ ያሉ የምስራቅ ሐረርጌ ከተሞችን የኃይል እጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፍ አስታውቀዋል።
የትራንስፎርመሩን ተከላ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚመለከታቸው የመስተዳድር አካላትና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ መቅረቡን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!