በሀረሪ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጥሪ ተከትሎ ከተለያዩ የአለም ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ሀገር ወዳድ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል እና በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቁቁን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ያሉ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በክልሉ በኩል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የእንግዶቹ ወደ ክልሉ መምጣትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና አሸባሪው ህወሓት በሀገር ላይ በከፈተው ጦርነት ምክንያት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲነቃቃ ከማድረግ አንፃር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ወደ ክልሉ የሚመጡ የዳያስፖራ ማህበረሰብ በቆይታቸው ጥሩ መስተንግዶና አገልግሎት እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት ከነዋሪው በተለይም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።
“የምንቀበለው በትግል ላይ የቆዩ ጀግኖችን ነው” ያሉት አቶ ሔኖክ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ ከሆቴል ቤቶችና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ ለሚኖራቸው ቆይታ ሆቴል ቤቶች ከ30 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አክለው ገልጸዋል።
ክልሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉት እና ለቱሪስት ምቹ ክልል መሆኗን ጠቅሰው ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እንደተጠናቀቀ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
እንግዶቹ በክልሉ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሳተፉ ዳያስፖራዎችም የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ምቹ ሁኔታዎችን ስለመፍጠሩም አንስተዋል።
ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንግዶች ወደ ክልሉ ሲመጡም በእንግዳ ተቀባዩ ህዝባችን ደማቅ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!