Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ዓመታት ማህበረሰቡን ከቤተ እምነቱ ለማላቀቅ የተሰራው ስራ ቀላል አልነበረም- የሃይማኖት መምህራን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዓመታት ማህበረሰቡን ከቤተ እምነቱ ለማላቀቅ የተሰራው ስራ ቀላል እንዳልነበረ የሃይማኖት መምህራን ተናገሩ።
ኡስታዝ አቡበክር አህመድና ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈሚካዔል በፋና ቴሌቪዥን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩረውና ስለ ኢትዮጵያ በተሰኘው ፕሮግራም ላይ “እሴቶቻችን ለአብሮነታችን” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ውይይት ላይ ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸው ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈ ሚካዔል፥ ሃይማኖተኛነት አንዱ እሴት ነው ያሉ ሲሆን ሃይማኖተኛ መሆናችን የሚታወቀውም በሃይማኖት እሴቶቻችን ነው ብለዋል፡፡
እሴቶቻችን ደግሞ የማንነት መገለጫዎች በመሆናቸው ይህን አጣን ማለት እራሳችንን አጣን ማለት ነውና ይንን የሚያሳጣን ነገር ሲመጣም እስከ መስዋዕት በመክፈል ግዴታ ልንጠብቀው ይገባል ነው ያሉት፡፡
የእኛን እሴት የሚሸረሽር፣ ወንድምን እንድንበድልና እንድንጎዳ የሚያደርግ መመሪያ ሲመጣም እኛን አይወክልም ማለት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም መተባበር እና ማንነታችንን መጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ኡስታዝ አቡበክር አህመድ በበኩላቸው እምነት ከዛም የምንኖርበት ባህል፣ አብሮነት፣ መተጋገዝ፣ መረዳዳት ማሳያዎቻችንና እኛን እንደ ሃገር የሚገልፁን እሴቶቻችን ናቸው ብለዋል።
እምነት ከውስጣችን ሲጠፋ ግን ስነምግባር እና እሴት አብሮ ይጠፋል ያሉ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜም ውስጣዊ ማንነት ይፈርሳል፤ በዚህም ምንም ነገር ከማድረግ አያግድንም፤ ሁሉም ነገር ገደብ የለሽ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት ማህበረሰቡን ከቤተ እምነቱ ለማላቀቅ የተሰራው ስራ ቀላል አይደለም ያሉት የሃይማኖት መምህሩ ለዚህም አሁን ላይ የተፈፀሙት ሃይማኖት ካለው ማህበረሰብ አይደለም ሃይማኖት የሌለው ማህበረሰቦች የማይሰሩት ናቸው ብለዋል፡፡
በሽብር ቡድኑ በከባድ መሳሪያ የተመቱና የወደሙ ቤተ እምነቶችን በማንሳት፤ ይህም እንደ ትውልድ የእኛ ኪሳራ ማሳያዎች ናቸው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሼክ ያሲንና ብፁ አቡነ ኤርሚያስን የመሰሉ ቅን ልብ ያላቸው አባቶች ደግሞ የእኛ እሴት መገለጫ የእምነት ማሳያዎች ናቸው ያሉ ሲሆን፥ የእነሱን ፈለግ መከተልና ሀገር እንደ እንደነሱ አይነት ትውልድን እንድታፈራ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ትውልድን የማዳን፣ የማነፅ፣ ግብረ ገብነት እንዲኖር መስራት ደግሞ ከቤተ እምነቶችና ከቤተሰብ ይጠበቃል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.