Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ በያዛቸው አካበቢዎች እንዲጸና የተደረገው የትግራይ ህዝብ በድጋሚ የጥሞና ጊዜ አግኝቶ የሽብር ቡድኑ ትክክለኛ ማንነት እንዲገነዘብ ለማስቻል ነው –  መንግስት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ“ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” የመከላከያ ሰራዊት በያዛቸው አካበቢዎች እንዲጸና የተደረገው የትግራይ ህዝብ በድጋሚ የጥሞና ጊዜ አግኝቶ የሽብር ቡድኑ ትክክለኛ ማንነት እንዲገነዘብ ለማስቻል መሆኑን መንግስት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፥ የትግራይ ህዝብ ልጆቹን ለተጨማሪ ጦርነት ከመማገድ እንዲቆጠብ መንግስት ያሳስባል ብለዋል።

በሽብር ቡድኑ ተወረው በነበሩና ከፍተኛ ውድመት በደረሰባቸው አካበቢዎችም ዜጎችን ለማቋቋም ሁሉም ሊረባረብ ይገባዋል ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፥ የትግራይ ህዝብ ዳግም የተሰጠውን ይህን እድል ሊጠቀምበት እና ምንም ያላተረፈበትን ጦርነት ሊያወግዝ ይገባል።

የትግራይ ህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉበት ይታወቃል ያሉት ዶክተር ለገሰ፥ መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ እንዲሆን ግን የትግራይ ህዝብ የሽብር ቡድኑን የጦርነት አባዜ መቃወም እንዳለበት አሳስበዋል።

ለሽብር ቡድኑ የስልጣን ጥም ሲል ልጆቹን ማስጨረሱን ከመቃወም አልፎ በተግባር እንዲታገልም ነው ሚኒስትሩ የጠየቁት።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በተለያየ የአለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ የ“አይዞን” ኢትዮጵያ እና  የ”በቃ” እንቅስቃሴን  በሚመለከት  ያከናወኗቸው ስራዎች ትልቅ ውጤት ያመጡ እና ወገንን የጠቀሙ በመሆናቸው ለመልካም ስራቸው መንግስት እንደሚያመሰግን አስታውቀዋል።

በሀገር ቤት ደግሞ አሁን ከተለያዩ የአለም ክፍሎች እየመጡ ያሉ ዳያስፖራዎችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ህዝቡ እየተቀበላቸው መሆኑ እንደሚያስደስት በመጥቀስ  ይህም  ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ ተወረው በነበሩና ከፍተኛ ውድመት በደረሰባቸው አካበቢዎችም ዜጎችን ለማቋቋም ሁሉም እንዲረባረብም ነው ያሳሰቡት።

 

በበርናባስ ተስፋዬ

 

 

 

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.