የገና በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲከበር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው-ፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም የገና በዓል የእምነቱ ተከታዮች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት፣ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበት፣ ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ መኖርንና መስራትን ለመላው የዓለም ህዝብ የሚያሳዩበት ታላቅ በዓል መሆኑን አውስቷል፡፡
ከሀዲው፣ አሸባሪውና ተላላኪው የህወሓት ቡድን የሀገር አንድነትንና እኩልነትን በማንአለብኝነትና በእብሪት በመዳፈር በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀሙ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጁንታውና ርዝራዦቹ የእጃቸውን እንዲያገኙ መደረጋቸውንም አመልክቷል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን መንግስት ለጥሞና እና ለሰላም የሰጠውን ዕድል ወደ ጎን በመተው በአማራና በአፋር ክልል መጠነ ሰፊ ወረራ ማካሄዱና በንጹሃን ላይ ግፍ መፈፀሙ እንዲሁም የህዝብና የመንግስት ተቋማትን ማውደሙ ይታወቃል፡፡
ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመሩት ዘመቻ “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ጁንታውንና ተላላኪው ሸኔን እንዲሁም ሌሎች ፀረ ሰላም ታጣቂዎችን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት በወረራ ከያዟቸው ቦታዎች ሁሉ በሽንፈት ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በየጦር ግንባሩ ካደረገው ፍልሚያ በተጨማሪ ወራሪው ኃይል በለቀቃቸው አካባቢዎች ዜጎችን የማረጋጋትና መልሶ የማቋቋም ተግባር ጎን ለጎን በአዲስ አበባና በሌሎች የአገራችን አካባቢዎችም የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በርካታ የጸጥታና የደህንነት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዚህም መሰረት ይህንን ታላቅ ኃይማኖታዊ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ያለምንም የፀጥታ ስጋት ያከብሩ ዘንድ ፖሊስ ሌት ተቀን ሳይታክት በፍጹም ቁርጠኝነት ተልዕኮውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ወደ ሀገር የገቡ ዳያሳፖራዎችን እና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበርም የፌደራል የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከምንጊዜውም በላይ በቂ ዝግጅት አድርጎና ስምሪት ወስዶ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል፡፡
ሰላም ወዳዱ ህዝብም እንደተለመደው ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ በማድረግ የፌዴራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!