የክልል መንግስታት ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረሪ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስታት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ባስተላለፈው መልዕክት÷የዘንድሮው የልደት በዓል ኢትዮጵያ በተለይም አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ያደረገችውን የመጀመሪያ ዙር የህልውና ዘመቻ በድል ባጠናቀቀችበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብሏል፡፡
ዘመቻ ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት በስኬት መጠናቀቅ በግንባር ከነበረው ጥምር-ጦር ባሻገር መላው ኢትዮጵያውያን ዘርፈ-ብዙ ተሳትፎና ድጋፍ አድርገዋል ነው ያለው፡፡
መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የተገኘውን ድል ወደ ዘላቂ ሠላምና ልማት ለመቀየር እየተደረገ ላለው ጥረት የበኩላቸውን በመወጣት እንዲሆንም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት÷የዘንድሮው የገና በዓል ሀገራችን የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ በመከተችበት የድል ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው አውስቷል፡፡
በዓሉ በተለይም የውስጥ ከሃዲዎችና እብሪተኞች ከውጭ ሃይሎች ጋር በመተባበር ሀገራችንን ለማፍረስ የወጠኑት ሴራ መላው ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ በመከቱበት ማግስት የሚከበር መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በጦር ግንባር ያሳየነው አንድነት በሽብርተኛው ቡድን በግፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን መንከባከብ እና መደገፍ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የሀገራችንን ሰላምና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማስከበር በተለያዩ ግንባሮች ላይ ተሰማርተው የሕይወት መስዋዕትነትን እየከፈሉ ለሚገኙት የጀግናው መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህንን በዓል ስናከብር ከምንጊዜውም በላይ ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነትና ልማት በቁርጠኝነትና በጋራ ቆመን የምንታገልበት ወቅት መሆኑን ነው የገለጹት።
የየክልሎቹ ማንግስታት በተለያዩ ግንባሮችና መስኮች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ፣ ማዕድ በማጋራት እንዲሁም በየአካባቢው የሚገኙና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በዓሉን አብሮ በማሳለፍ ወገናዊ አጋርነቱንን እንዲተገብርም ለህብረተሰቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡