Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት ይጠበቅበታል – ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳያስፖራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በህልውና ትግል ላይ መሆኗን በማሰብ፥ ለአገራዊ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት እንዳለበት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ አሳሰቡ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት፥ በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ላይ ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ስለሚጠበቁ እንቅስቃሴዎች በኢንተርኔት የዙም ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የተሳተፉት ዶክተር መሐመድእንድሪስ ፥ ኢትዮጵያን ለታደጓት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ በተለያየ ዘርፍ ትግል ላደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ፈተና ውስጥ ያስገቡ ጫናዎች እንደነበሩ ያነሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ አሁን ወደ መልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራ መገባቱንም ነው ያመላከቱት።

የዳያስፖራው ማህብረሰብ በህልውና ትግሉ ወቅት ከፍተኛ የዜጋ ዲፕሎማሲን ያበረከተ እና ኢትዮጵያ ያለባትን የዲፕሎማሲ ክፍተቶች ያሟላ ሚና ነበረው ብለዋል።

በሀብት ማሰባሰብ ረገድም ዳያስፖራው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች እና ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከምንጊዜውም በላይ ገንዘቡን እየለገሰ መሆኑን ጠቅሰው ÷ሆኖም ዳያስፖራው ካለው አቅምና ፍላጎት አንፃር አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ነው ያስረዱት።

በተለይ በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ከፍተኛ ሥራዎች መኖራቸውን በመጠቆም በተለይ በትምህርት፣ በጤና፣ በማህበረሰባዊ መልሶ ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ስራዎች ይጠብቁናል ብለዋል።

የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበሩት ዳያስፖራ ጥምረት ፕሬዚደንት አቶ አለባቸው ደሳለኝ በበኩላቸው ፥ በአሸባሪው ህወሓት የደረሱ አጠቃላይ ጉዳቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም መንግሥት የጀመረውን ጥረት ዳያስፖራው በሙሉ አቅሙ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ዳያስፖራው በዘላቂነት ሀገርና ህዝብን በሙያውና በገንዘቡ እንዲረዳ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.