Fana: At a Speed of Life!

መርማሪ ቦርዱ በተጠርጣሪዎች ሰብአዊ አያያዝ ላይ ይበልጥ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በተጠርጣሪዎች ሰብአዊ አያያዝ ላይ ይበልጥ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳሰበ፡፡
 
ቦርዱ ሰሞኑን በሶማሌ እና በሐረሪ ክልሎች በመገኘት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ ግለሰቦች ሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ምልከታ አድርጓል፡፡
 
የቦርዱ አባላት በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን አይሻ እና ሌሎች ወረዳዎች እንዲሁም በሀረሪ ክልል ፖሊስ መምሪያና በክልሉ ፓሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በመገኘት ተጠርጣሪዎች ያረፉባቸውን ቦታዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
 
ከየማረፊያ ቤቱ ከተውጣጡ የተጠርጣሪዎች ተወካዮች ጋር በሰብአዊ አያያዝ፣ በውሃ፣ ምግብ፣ ህክምና፣ በመፀዳጃ ቤትና የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ዙሪያ እንዲሁም በቤተሰብ ስለመጠየቃቸው በተናጠል ተነጋግረዋል፡፡
 
በተመሳሳይም ቦርዱ ከሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የስራ ኃላፊዎች፣ ከሐረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ኦርዲን በድሪ፣ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና በየደረጃው ካሉ የሥራ እና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋርም ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
 
በውይይቱ ማብቂያ ላይም በሰብአዊ አያያዝ ዙሪያ አዋጁን ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ ክልሎቹ በጥንካሬ የፈጸሟቸውን እና በቀጣይ ቢታዩ በሚል የለያቸውን ጉዳዮች በማጠቃለያ ግብረ መልሶቹ አመላክቷል፡፡
 
ግብረ መልሱን ያቀረቡት የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ፥ ክልሎቹ የሰላምና የፀጥታ ስጋት ይሆናሉ በሚል የጠረጠሯቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን፣ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል ተገቢውን ማጣራት ተደርጎ ብዙዎቹ መለቀቃቸውን፣ የምግብና የውሀ አቅርቦት መኖሩን፣ ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቁ መደረጉን በጠንካራ አፈጻፀም አንስተዋል፡፡
 
አያይዘውም በበሽታ የተያዙ ሰዎች ሲገኙ ወደ ሌሎች እንዳይዛመት በፍጥነት ለይቶ ለብቻ ማቆየት መቻሉን እና በፖሊሶች በኩል ቀናነት መኖሩንም በጥንካሬ ካነሷቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
 
በሌላ በኩል በቤተሰቦቻቸው የማይጠየቁ ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቁ ቢደረግ፣ አሁንም ጤነኛ እና ጤነኛ ያልሆኑት ተጠርጣሪዎች በፍጥነት ተለይተው ለብቻቸው የሚሆኑበት ሁኔታ ቢመቻች፣ የምርመራ ሂደቱን በማፋጠን ጥፋተኛ የሆኑት እና ጥፋተኛ ያልሆኑት ቢለዩ እንዲሁም ቦታዎቹ ምቃታማ በመሆናቸው የተጠርጣሪ ማረፊያዎች ሰፋ ያሉ ሆነው ቢመቻቹ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
የሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፥መርማሪ ቦርዱ የአዋጁን አፈፃጸም በተመለከተ በክልሉ ያካሄደው ምልከታ ክልሉን ይበልጥ የሚያበረታታ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
 
ቦርዱ የሰጣቸውን ግብረ-መልሶችም በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ትልቅ ግብአት እንደሚሆን መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.