በኦሮሚያ በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ 876 የሚሆኑ የሸኔ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014፣ (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የህልውና ዘመቻው ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት ማምጣቱን የክልል የመንግስት ገለፀ።
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ በክልሉ የልማትና የፀጥታ ስራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአሸባሪውን ሸኔ አጥፊ ቡድን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተቀላቀሉ ወጣቶች ከአባገዳዎች ጋር በመነጋገር 312 ወጣቶች እጅ እንዲሰጡ መደረጉ ተነግሯል።
የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ባለው ስራም በሁለት ሳምንት ብቻ 876 የሚሆኑ የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱም በመግለጫው ተነስቷል ።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወዲህም ከ2 ሺህ 400 በላይ የቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ፥ በህብረተሰቡ ጥቆማ 540 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው።
የአካባቢ ጥበቃ ስራን በተመለከተም፥ ለምርትና ምርታማነት ወሳኝ ሚና የሚጫወተው የአካባቢ ጥበቃ ስራ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በነገው እለት በይፋ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
በክልሉ የመኸር ምርትን የመሰብሰብ ስራው ጋር ተያይዞ በአመርቂ ሁኔታ መከናወኑን ነው ሃላፊው ያነሱት።
በዚህም 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ላይ ከተዘራው ሰብል እስካሁን 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል።
በመስኖ ስንዴ ልማት ዘርፉም 350 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቀዶ እስካሁን 302 ሺህ ሄክታር ማልማት መቻሉን አንስተዋል።
ለተፋሰስ ልማቱም ቦታዎች መለየታቸውን ገልጸው ፥ ነገ የልማት ስራው በይፋ ይጀመራልም ነው ያሉት።
በዝናብ እጥረት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።
በሀብታሙ ተ/ስላሴ እና አፈወርቅ አለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!