በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከስረ መሰረቱ ለመፍታት የእስረኞችን ክስ ማቋረጥ አስፈልጓል- የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከስረ መሰረቱ ለመፍታት የእስረኞችን ክስ ማቋረጥ አስፈላጊ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ አገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኋን ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጀግኖች ሰማዕታትን የመዘከር፣ ዕውቅናና ሽልማት መስጠትን
ይህን በተመለከተ የኢትዮጵያን ህልውና በመታደግ ውድ ህይወታቸው ለገበሩ፣ ከፍተኛ አበርክቶ ለነበራቸው የምንጊዜም ጀግኖችን የመዘከር፣ ዕውቅናና ሽልማት ከመስጠት በኩል፤ መንግስት ከወታደራዊ ማዕረጎችና ኒሽኖች በተጨማሪ ለሀገራቸው ውድ ዋጋ ለከፈሉና ጉልህ አበርክቶ ላሳዩ ጀግኖች ብቻ የሚሰጠውን የጥቁር አንበሳና የዓድዋ የመጨረሻ ከፍተኛ ሜዳሊያ እንዲሸለሙ ማድረጉን ነው የገለፁት።
በተጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም የመከላከያ ሰራዊት እጅግ በርካታ ተግባራት ቢፈፅምም ሀገሪቱ ካለችበት ጂኦፓለቲካዊና ውስብስብ የፀጥታ እንዲሁም የተለያዩ ስጋቶች አኳያ ራሱን የማዘመን፣ የማደራጀትና ልቆ ለመገኘት የሚያበቃውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።
እየተሰነዘሩብን ያሉ ጥቃቶችም ገና እልባት አላገኙም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ታሪካችንን፣ የህዝቦቻችንን ፍላጎትና የምንመኘዉን አይነት ህብረ ብሔራዊና ሉዓላዊ አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል ግንባታ ማካሄድ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ህዝቡም ይህን ተገንዝቦ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ የመከላከያ ሰራዊቱና የክልል የፀጥታ አካላት የገነቡትን አብረው መስዋዕት የመሆንና ተቀናጅቶ ሀገርን የመከላከል ስራ ይበልጥ ማጎልበት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
የተወሰኑ እስረኞች ክስ መቋረጥ
የተወሰኑ እስረኞች ክስ መቋረጥን በተመለከተ ዶክተር ለገሰ፥ ከፖለቲካ ልሂቃን አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እየተንጸባረቁ ያሉ ያለመግባባት ችግሮችን በሃገራዊ ምክክር ከስር መሰረቱ ለመፍታት በመደበኛ ፍትህ ብቻ ሳይሆን በተሃድሶ የሽግግር ማዕቀፍ ጭምር እልባት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን መንግስት ያምናል ነው ያሉት።
መንግስት እንደ አንድ ተዋናይ ለአካታች ምክክር መድረኩ የተመቻቸ ፖለቲካዊ ሁኔታን መፍጠር እንደሚጠበቅበት በማንሳት፥ ለስኬታማነት መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ መክፈልም ይገባል ብለዋል።
ዘላቂውን ህዝባዊና ሀገራዊ ጥቅሞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለአገራዊ ምክክሩም አካታችነትና ስኬት ሲባል በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ህጋዊና ተቋማዊ አሠራርን በጠበቀ አኳኃን መፍታት ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ የተወሰኑ እስረኞች ክስ መቋረጡን ነው ያመለከቱት።
የክስ መቋረጥ ውሳኔ ሁለት መሰረታዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ያለመ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የመጀመሪያዉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ማህበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ከእልህና ከመጠፋፋት ፖለቲካ በራቀ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ሊያረጋግጥ በሚችለው በሀገራዊ አካታች ዴሞክራሲዊ ስርዓት ለመፍታት ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታን ለመፍጠር መሆኑን ዘርዝረዋል።
በሁለተኛነትም ዋስትና ያለዉ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና፣ ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት እና ሉአላዊ አንድነትን ከአደጋ ለመታደግ ተብሎ የተወሰደ ፖለቲካዊ እርምጃ መሆኑንም አስረድተዋል።
የውሳኔው ድንገተኛነትና ከውሳኔው በኃላ የታዩ አዝማሚያዎች
በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡ የተለያዩ ሀገራት መንግስታት ተሞክሮ መንግስትና ህዝብ በማህበራዊ ኮንትራት የሚሰሩ መሆኑን ያሳያል ያሉት ዶክተር ለገሰ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ ባካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግስት መሆኑንን ይህ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የህዝብ ውክልና ያለው፤ ህግና ስርዓትን ተከትሎ የሚሰራ በምልአተ ህዝቡ ጥቅሞች፣ በህብረ-ብሔራዊ፣ ሉዓላዊ አንድነትና በህግ የበላይነት የማይደራደር መንግስት ነው ብለዋል።
ተግባሮቹም ሆነ የሚወስናቸው ጉዳዮች የሀገርና የህዝብን ዘላቂ ጥቅሞች፤ አስተማማኝ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲረጋግጡ አበክሮ እንደሚሰራ በመግለጽ፥ መንግስት ካለፉት ልምዶች በመነሳት ጠንካራ ተቋማት እየገነባ መሆኑንና ተቋማቱም ነፃ ሆነው ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል በማድረግ ውሳኔዎችን እያሳለፉ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።
ካለፉት ቁርሾዎቻችንና ካሳለፍናቸው መከራዎች አኳያ በመንግስት ሰሞነኛ ውሳኔ ላይ ጥርጣሬዎች መነሳታቸው ተገቢ አይደለም ባይባልም ከራሱ ከመንግስት ባህሪ ህዝባችን እምነቱን ማሳደር አለበት ብለዋል።
መንግስት ጠንካራ ነፃ ተቋማትን እየገነባ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ትክክለኛ የመንግስት ባህሪን መላበስ እንዳለበት በማመላከትም ባለው ማህበራዊ ኮንትራት የህዝብና ብሄራዊ ጥቅሞችን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን ያለ ምንም ጫና መወሰንና መተግበርና ለዉሳኔዎቹም ሙሉ ሃላፊነት መውሰድ አለበት፤ ይህ የዲሞክራሲያዊ መንግስት መርህ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በቀጣይ ለአካታች ብሄራዊ ውይይቶቹ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለማስፋን በሚወሰዱ የፖለቲካ እርምጃዎች ዙሪያ አመራሩ ጊዜ ወስዶ እንደ ፓርቲም እንደ መንግስትም በመሰረታዊ መርሆዎቹና አቅጣጫዎቻቸዉ ላይ ሰፋፊ ውይይቶችን ማድርጉን ዶክተር ለገሰ አስታውቀዋል።
ለሃገራዊ አካታች ምክክሩ ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የተወሰኑ እስረኞች ክስ መቋረጥ እንደሚገባም በአመራሩ መካከል ስምምነት አለ ነው ያሉት፡፡
ከፌደራል እስከ ወረዳ ያለው አመራርና የመንግስት ሰራተኛ ሳይቀር በእነዚህ መርሆዎች ላይ መምከራቸውንና በመጨረሻም ከነዚህ ወገኖች የተገኘውን ግብረ-መልስ መሰረት አድርጎ በህግ ስልጣን የተሰጠው አካል የመጨረሻ ውሳኔ መስጠቱን ግልፅ አድርገዋል።
ከዚህ አኳያ በተወሰነ አካል ብቻ የተወሰነ ውሳኔ ተደርጎ የሚወራው ወሬም መሰረተ ቢስ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ክሱ ሲቋረጥ እነዚህ ግለሰቦች ግጭት ሊቀሰቅሱ ይችሉ ይሆን?
መንግስት ክስ አቋረጠ እንጂ ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነፃ ናቸው አልተባለም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ወገኖችም ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው የተሻለ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲችሉ ዕድል የተሰጣቸው ስለሆነ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን ይክሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
መንግስት ያለፉ ዋጋ እስከፋይና ግጭት ጠማቂ አካሄዶችን በጭራሽ እንዲደገሙ አይፈቅድም በማለትም፥ በእነዚህ ጉዳዮች መንግስት ድርድር እንደሌለው ግልፅ አድርገዋል።
ዕድሉን ያገኙ አካላት በአግባቡ ከተጠቀሙበት ሀገር ይጠቀማል፤ ዕድሉን ካበላሹ ደግሞ የመጀመሪያው ተጎጂ ራሳቸውና እንቆምለታለን ያሉት ማህበረሰብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡም የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት አሳስበዋል።
ውሳኔው ያገኘነውን ድል የሚያደበዝዝ ሳይሆን ለዘላቂ ድል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነ በማመልከት፥ የውሳኔውን መነሻና ፋይዳ በሰከነ መልኩ ሲፈተሽ ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም መረጋገጥ የሚያግዝ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚቀንስ፤ በአውደ ውጊያ የተገኘውንም ድል በሰላሙ መድረክ እንዲደገም የሚያደርግ፤ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!