Fana: At a Speed of Life!

“ሂሩት አባቷ ማን ነው?” ፊልም ከ57 ዓመት በኋላ ተመርቆ ለዕይታ በቃ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1957 ዓ.ም “ሂሩት አባቷ ማን ነው?”በሚል ርዕስ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለጥቁርና ነጭ ፊልም ከ57 ዓመት በኋላ ተመርቆ ለእይታ በቅቷል፡፡

ፊልሙ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በይፋ ተመርቆ በዛሬው ዕለት ለዕይታ በቅቷል፡፡

ከንቲባ አዳነች “ሂሩት አባቷ ማን ነው?” በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ፊልም ብቻ ሳይሆን÷ ከዚያ በኋላ ለመጡት የጥበብ ስራዎች ሁሉ መነሻ መሆን የቻለ፤ አይን የገለጠና በርካታ የጥበብ ሰዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነ ታሪካዊ ስራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን ሥራ የጀመረችው ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ቀደም ብላ ቢሆንም በፊልሙ ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን ዛሬ ላይ ደርሳለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎችና ቋንቋዎች እና እሴቶች አገር ስትሆን አሸባሪው ቡድን ይህንን አብሮነት ለማፍረስ ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ከንቲባዋ አውስተዋል።

ኪነጥበብን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያነሱት ከንቲባ አዳነች፥ የኪነጥበብ ስራዎቻችን የኢትዮጵያዊያንን አብሮነትና አንድነት የሚያጎላ ለሀገራችን የትንሳኤ ጉዞ የሚያግዝ ትልቅ አቅም መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእዳ ተይዞ የነበረውን ፊልም በጥንቃቄ ይዞ በማቆየት እና ለዚህ በማብቃቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አሁንም ለፊልሙ ኢንዱስትሪ ብድሮች እንዲመቻች ጥሪ ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በስነ ስርዓቱ ላይ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የተለያዩ ባለሙያዎች እውቅና ተበርክቶላቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.