ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ጥር12፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የጤና ሚኒስቴርና የግብርና ሚኒስቴር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገለጹ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ6ተኛ ጊዜ፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው “የአንድ ጤና ቀን” (One Health Day) በዓል በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፥ ከፍተኛ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ነው በአዲስ አበባ እየተከበረ ያለው ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የ”አንድ ጤና መርህ” ተግባራዊ የሚደረግበት አንዱ አላማ በሰው፣ በእንስሳት እና በአካባቢ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ተመጋጋቢነት እንዳላቸው ለማስገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም፥ የሕብረተሰቡን ጤና የሚያውኩ ችግሮችን ከማስወገድ አንፃር በግብርና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የውሻ በሽታን ለማስወገድ እየተደረገ ያለውን የክትባት ዘመቻ አድንቀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው፥ ግብርና ሚኒስቴር ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በ”አንድ ጤና መርህ” ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ፍቅሩ አያይዘውም ከተሰሩ ስራዎች መካከል ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ከሚችለው አንዱ የውሻ እብደት በሽታ ክትባት ዘመቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ሲሳይ ጌታቸው በበኩላቸው፥ በአሁን ሰዓት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ስርጭት አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው፥ ችግሩን ለመቅረፍ “የአንድ ጤና መርህ” ስርዓትን መከተል ወሳኝ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!