Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ወሎ ዩኒቨርሲቲንና ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ተዘዋውረው ተመለከቱ።
 
በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ወሎ ዩኒቨርሲቲን በመጠገን በሚቀጥለው ወር የመማር -ማስተማር ሥራውን በከፊል እንደሚጀምር ተገልጿል።
 
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የደሴ ሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አሸባሪው ህወሓት በዩኒቨርሲቲውና በሆስፒታሉ ያደረሰውን ጉዳት በአምባሳደሩ ለተመራው የልዑካን ቡድን ገለጻ አደርገዋል፡፡
 
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈፀመበት ወቅት የዩኒቨርሲቲውን የተለያዩ ንብረቶች ዘርፎ መውሰዱንና ያልቻለውንም ማውደሙን ለልዑኩ አስረድተዋል።
 
አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ዩኒቨርሲቲው መልሶ እንዲቋቋም ድጋፍ እንናደርጋለን ማለታቸውን ዶክተር መንገሻ ገልጸዋል።
 
በፈረንሳይ ካሉ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር የቴክኖሎጂና የአሰራር ልምድ ልውውጥ እንዲደርግ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።
 
ዶክተር መንገሻ እንዳሉት፥ በአምባሳደሩ የተመራ ልዑክ የተቋሙን ጉዳት ተዘዋውሮ መመለክቱ የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ጥፋት ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ይረዳል።
 
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ተቋማትንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ተቋሙን መልሶ ለማደራጀትና የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር መንገሻ ተናግረዋል።
 
 
“የሽብር ቡድኑ በዘመናዊ መንገድ የተደራጀውን ቤተሙከራ፣ ቤተ መጻህፍት፣ አይ.ሲ.ቲ፣ የመምህራንና የተማሪዎች መኖሪያ፣ የመማሪያና መመገቢያ ህንፃዎች ላይ ጉዳት ቢያደርስም ተጠግነው ለሥራ ዝግጁ እየሆኑ ይገኛሉ” ብለዋል።
 
የኤሌክትሪክና የውሃ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ሌሎች ለመማር ማስተማር ሥራው የሚያስፈልጉ ግብአቶች እየተሟሉ መሆኑንም አመልክተዋል።
 
“በየካቲት ወር መጀመሪያ የሕክምና ተማሪዎችን ተቀብለን ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እያረግን ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ በወሩ መጨረሻ ደግሞ ሌሎች ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
 
በተመሳሳይ የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ እንዳሉት፥ ሆስፒታሉ ለምስራቅ አማራ፣ አፋርና ከፊል ትግራይ ህዝብ ተደራሽ ሆኖ ሲገለግል የነበረ ቢሆንም በሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ነው የወደመው።
 
ዶክተር ሃይማኖት እንዳስታወቁት፤ ሆስፒታሉ በቅንጅት በተከናወነው ሥራ በአሁኑ ወቅት በከፊል ተስተካክሎ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል።
 
የፈረንሳይ አምባሳደር ለሆስፒታሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ነው ዶክተር ሃይማኖት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደነበሩት ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
 
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.